የአፍሪካ ህብረት እና ኢጋድ በኢትዮጵያ እየተዋጉ ያሉ ወገኖችን እንዲያሸማግሉ የአፍሪካ ልሂቃን ጠየቁ
ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ያሳሰባቸው 60 የሚጠጉ የአፍሪካ ልሂቃን፤ የአፍሪካ ህብረት እና የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) በሀገሪቱ ውጊያ የገጠሙ ኃይሎችን የማሸማገል ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠየቁ። የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ ተመራማሪዎች፣ ደራሲዎች እና የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች የተካተቱበት የልሂቃኑ ስብስብ ጥያቄውን ያቀረበው፤ ትላንት ሐሙስ ለሊት ይፋ በተደረገ ግልጽ ደብዳቤ ነው።
ደብዳቤውን ከፈረሙ ምሁራን መካከል የካናዳው ዊልፍሪድ ላውሪየር ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ማርታ ኩዌ ኩምሳ፣ የአሜሪካው ፔንሲልቫኒያ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዳግማዊ ውብሸት፣ የካሊፎርኒያው ኩዊንስ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር አወት ወልደሚካኤል ይገኙበታል። እንደ ካሜሮናዊው ፈላስፋ፣ የፖለቲካ “ቲዮሪስት” እና የአደባባይ ምሁር አቺሌ ሜምቤ እና ሴኔጋላዊው ደራሲ እና ጋዜጠኛ ባቡባከር ቦሪስ ዲዮፕ ያሉ እውቅና ያላቸው ልሂቃን በደብዳቤው ፈራሚነት ከተጠቀሱ 58 አፍሪካውያን ባለሙያዎች ዝርዝር ውስጥ ተካትተዋል።
አፍሪካውያኑ ልሂቃን በዚሁ የጋራ ደብዳቤያቸው፤ በፍጥነት እያሽቆለቆለ ነው ያሉት የኢትዮጵያ ሁኔታ “ሐዘን እና ድንጋጤ” እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ያለውን ውጊያ “የእርስ በእርስ ጦርነት” ሲሉ የጠሩት ባለሙያዎቹ፤ ውጊያው በአፍሪካ የሚቀሰቀሱ ግጭቶችን እንዴት መፍታት እንደሚገባ የአፍሪካ ምሁራን ያቀረቧቸውን የተትረፈረፉ ሃሳቦች ግልጋሎት ላይ ላለማዋላቸው ማሳያ ነው ሲሉ ጽፈዋል።
ዘገባው የ"ኢትዮጵያ ኢንሳይደር " ነው።
ምንም አስተያየቶች የሉም