Ticker

6/recent/ticker-posts

በአማራ ክልል ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው እህል ወደመ



በአማራ ክልል ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው እህል ወደመ 


በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ ግድም ወረዳ በማጀቴ አካባቢ ነዋሪ በሆኑ አርሶ አደሮች ማሳ ላይ ረቡዕ ሌሊት  በተፈጸመ ድንገተኛ ጥቃት ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ  የሚገመት እህል መቃጠሉ ተገለጸ።


ኢ.ፕ.ድ. ከሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረጻዲቅ አገኘሁት ባለው መረጃ እንዳስነበበው፤ ከወቅታዊ የአገሪቷ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በዞኑ ስጋቶች ስለነበሩ እንደ ዞን አቅጣጫ ተሰጥቶ የተለያዩ የጸጥታና ደህንነት ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይቷል፡፡

 


በዋናነትም ከአርሶ አደሩ አንጻር የተሰበሰቡ ሰብሎች ማሳ ላይ እንዳያድሩና ከአደሩም ስምሪት ተሰጥቶ እንዲጠበቁ ሲደረግ ቆይቷል። 


ይሁን እንጂ ከትላንት በስቲያ ጥቅምት 3 ቀን 2014 ዓ.ም ለጊዜው ምክንያቱ ባይታወቅም አደጋው በደረሰበት እለት ተረኛ የነበሩና የጥበቃ ስራን እንዲያከናውኑ ሃላፊነት የተሰጣቸው አካላት በስፍራው እንዳልተገኙ አረጋግጠናል፤ ይህንን ክፍተት ተጠቅመው ማንነታቸው ያልታወቀ ጉዳት አድራሾች የአርሶ አደሮችን ሰብል አቃጥለዋል ነው ያሉት አቶ ታደሰ። 



የተሰበሰበውን የአርሶ አደሮች ሰብል  በማን ተቃጥሎ እንደወደመ እስካሁን አለመታወቁ የገለፁት ዋና አስተዳዳሪው፤ በዞን ደረጃ የተለያዩ መረጃዎች እየደረሱ ቢሆንም  ትክክለኛውን መረጃ ለማጣራት  የአጎራባች ወረዳ አካላትና መርማሪ የፖሊስ አባላት የተቀናጀ የምርመራ ሥራ እያከናወኑ መሆኑን አስታውቀዋል።


የዞን፣ የክልል እንዲሁም የፌደራል አመራሮችና የጸጥታ አካላት መከላከያን ጨምሮ በቦታው እንደተገኙ የጠቀሱት አቶ ታደሰ፤ የጉዳት መጠኑን ለማወቅ በተደረገው ጥረት  እስካሁን ባለው መረጃ ከ95 ኩንታል በላይ ጤፍ እንደተቃጠለና ይህም  በብር ሲገመት ግማሽ ሚሊዮን ብር እደሚደርስ አብራርተዋል።



የማጀቴ  ከተማ መሪ ማዘጋጀ ህንጻ ሹም ሃላፊ የሆኑት አቶ ያለው አየለ በበኩላቸው ጥቃት አድራሾቹ "የኦነግ ሸኔ" ታጣቂ አባላት ናቸው ብለዋል። 


ታጣቂዎቹ በአካባቢው ላይ ጥቃት ሲፈጽሙ የመጀመሪያቸው እንዳልሆነም ነው አቶ ያለው ያስታወቁት። 


እንደ አቶ ያለው ገለጻ፤ በአሁኑ ጥቃት የበርካታ አርሶ አደሮች የጤፍ ክምር ተቃጥሏል። ይህም በገንዘብ ሲተመን ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ይደርሳል። 


በቀጣይ ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር በጊዜያዊነት አካባቢውን ሀላፊነት ያለባቸው አካላት ተውጣጥተው እንዲጠብቁ፤ የሰላም ኮሚቴዎች በጋራ እንዲሰሩ፤ የደረሱ ሰብሎች በፍጥነት እየተነሱ ከተቻለ ወደ ጎተራ ካልተቻለ ደግሞ በቅርብ ርቀት ተጓጉዞ የሚወቁበትን ሁኔታ እየተመቻቻ መሆኑን የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገልጸዋል።


በትናንትናው እለትም በርከት ያሉ ሰብሎች ከማሳ ላይ መነሳታቸውን ዋና አስተዳዳሪው  አብራርተዋል፡፡

አስተያየት ይለጥፉ

0 አስተያየቶች