Ticker

6/recent/ticker-posts

በአርሲ ነገሌ ከ20 በላይ ካህናትና የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት መታሰራቸው ተነገረ



በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ሰሞናዊ ጉዳይ ምክንያት በአርሲ ነገሌ ከተማ ከ20 በላይ ካህናት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላትና ምዕመናን መታሰራቸውን በቦታው የሚገኙ የአዲስ ማለዳ ምንጮች ተናግረዋል፡፡


አርብ ጥር 26/2015 ከከተማው አስተዳደር እንወያይ የሚል ጥሪ ደርሷቸው የሄዱ የከተማው የቤተ ክህነት አመራር የሆኑት ቀሲስ ዮሐንስና ቀሲስ ማስረሻን ጨምሮ ከ20 በላይ የሆኑ የቤተክርስትያናት አስተዳዳሪዎች፣ ካህናትና የሠንበት ትምህርት ቤት አባላት ከአርብ ዕለት ጀምሮ በእስር ላይ እንደሚገኙ ተሰምቷል፡፡ 


በዕለቱ ለካህናቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ያወገዘውን ቡድን ተቀበሉ የሚል መመሪያ ከከተማ አስተዳደሩ እንደተላለፈላቸውም ተሰምቷል፡፡


ይህንንም አንቀበልም ያሉት የቤተ ክህነት አመራሮች ከቤተክርስትያን አስተዳዳሪዎችና ከሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ጋር እንዲታሰሩ መደረጉን የአዲስ ማለዳ ምንጮች ተናግረዋል፡፡


ቅዳሜ ጥር 27/2015 የቤተክርስትያንን ጥሪ በመቀበል በከተማው በሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስትያን የተሰባሰቡ ምዕመናንን በመክበብ ከቤተክርስትያን ለማስወጣት እንደተሞከረ የተናገሩት ምንጮች፣ በኦሮሚያ ልዩ ሀይል አባላት ምክንያት በቤተክርስትያኑ ለሚገኙ ምዕመናን ምግብና ውሀ ማድረስ አለመቻሉንም ተናግረዋል፡፡


በቤተክርስትያን ውስጥ ያሉ ምዕመናን ለውይይት አምስት ሰዎችን እንዲያቀርቡ በጸጥታ ኃይሎች መጠየቃቸውም የተሰማ ሲሆን፣ ምዕመናኑ በእስር ቤት ያሉ ካህናት እነሱን ወክለው መወያየት እንደሚችሉና የእነርሱ ድርሻ ግን ቤተክርስትያንን መጠበቅ እንደሆነ ተናግረዋል ተብሏል፡፡


ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያንን ለመጠበቅ ግቢ ውስጥ ያሉ ምዕመናን እስከ ትናንት ሰኞ ጥር 29 ቀን 2015 ድረስ አስፈላጊ የሆነ ምግብና ውሀ እያገኙ እንዳልነበረም ተነግሯል፡፡ 


ይሁንና እነዚሁ ምዕመናን ከትናንት ጥር 29/2015 ጀምሮ፤ ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ በልዩ ሀይል አባላቶቹ የተፈቀደላቸው ሲሆን፤ ነገር ግን ለአገልግሎት ወደ ቤተክርስቲያኗ የገቡ ካህናት አሁንም በቤተክርሲቲያኗ ውስጥ እንደሚገኙ አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች።


በአካባቢው የመከላከያ ሰራዊት አባላትም እንደሚገኙ የተናገሩት ምንጮች፤ ሁኔታዎችን ከመመልከት የዘለለ ሚና እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡


ከቤተ ክርስትያን ግቢ ውጭ ያሉና በትናንትናው ዕለት ጥቁር ልብስ ለብሰው ወደ ቤተክርስትያን የሄዱ ምዕመናን እንደታሰሩም ተሰምቷል፡፡ 


እስር ቤት ውስጥ ለሚገኙ ካህናትና ምዕመናን ከቤተሰቦቻቸው ምግብ እየሄደላቸው የነበረ ሲሆን፣ ምግቡ እየደረሰላቸው መሆኑን ማረጋገጥና ደህንነታቸውን ማወቅ አለመቻሉ ተነግሯል፡፡ ከትናንት ጠዋት ጀምሮ ደግሞ ለታሳሪዎች ምግብ ማስገባት መከልከሉም ተገልጿል፡፡


አርሲ ነገሌ ከተማ የአገረ ስብከት መቀመጫ ባትሆንም፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን የተወገዘው ቡድን ቅዳሜ ዕለት በከተማዋ በመገኘት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን ለመግባት መሞከሩ ተነግሯል፡፡ 


ከዚሁ ጋር በተያያዘም በሻሸመኔ ከተማ ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስትያን ከቅዳሜ ጀምሮ በተፈጠረው ችግር የተገደሉ ምዕመናንን አስከሬን ማግኘት እንዳልተቻለ የሻሸመኔ የአዲስ ማለዳ ምንጮች ተናግረዋል፡፡ 


የአዲስ ማለዳ መረጃ እንደሚያሳየው በትክክል የተመዘገበ የሟቾችን ቁጥር ማግኘት ባትችልም ልጆቻቸው ተገድለውባቸው አስከሬናቸውን ማግኘት ያልቻሉ ወላጆች እንዳሉ ሰምታለች፡፡ 


በጥይት ተመትተው ሆስፒታል ውስጥ የገቡ ምዕመናንንም መጠየቅ እንዳልተቻ ተሰምቷል፡፡


በቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስትያን ምንም አይነት አገልግሎት እንዳይኖር በጸጥታ ኃይሎች መታገዱን የተናገሩት ምንጮች፣ የጸጥታ ኃይሎች በከተማው በፓትሮል የታገዘ ቅኝት በማድግ ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

አስተያየት ይለጥፉ

0 አስተያየቶች