በኦሮሚያ 29 ሰዎች መገደላቸውንና ከ40 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን ኢሰመኮ ገለፀ።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በምስራቅ ወለጋ ዞን፣ ኪራሙ ወረዳ የሚገኙ ሲቪል ሰዎች ለደኅንነታቸው አስጊ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ናቸው ብሏል።
ኮሚሽኑ በኪራሙ ወረዳ፣ ቦቃ ቀበሌ መስከረም 7 እና 8 ቀን 2014 ዓ.ም በደረሱ ሦስት ተያያዥ ጥቃቶች በአጠቃላይ 18 ሲቪል ሰዎች መገደላቸውን ገልጿል።
በተመሳሳይ መስከረም 8 ቀን 2014 ዓ.ም በውልማይ ቀበሌ በተፈጸመ ሌላ ጥቃት 11 ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለኮሚሽኑ አሳውቀዋል።
በኪራሙ ወረዳ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ከተለያዩ የወረዳው አካባቢዎች ተፈናቅለው በኖሌ ቀበሌ፣በሀሮ እና ኪራሙ ከተሞች ተጠልለው የሚገኙ ከ40 ሺህ በላይ የሚሆኑ ነዋሪዎች ለወራት አስቸኳይ ሰብአዊ እርዳታና ሌሎች ድጋፎችን ባለማግኘታቸው አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ነዋሪዎች ነግረውኛል ብሏል ኮሚሽኑ።
ኪራሙ ወረዳን ከቡሬና ነቀምቴ ከተሞች ጋር የሚያገናኙ ዋና ዋና መንገዶች ለተሸከርካሪ እንቅስቃሴ ተዘግተው እንደሚገኙ ኮሚሽኑ አረጋግጧል።
ኢሰመኮ የፌዴራልና የክልሉ መንግስት የፀጥታ ኃይሎች በኪራሙ ወረዳ ላለው የፀጥታ ስጋት ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት እና በነዋሪዎች ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት የሚያደርሱ ኃይሎችን ከሕግ ፊት ለማቅረብ ተጨባጭ እርምጃዎችን እንዲወስዱ አሳስቧል።
በተጨማሪም "በግጭቱ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደ ቀያቸው መመለሱ እንደተጠበቀ ሆኖ ተፈናቃዮቹ ለከፋ የሰብአዊ ቀውስ ከመጋለጣቸው በፊት በአፋጣኝ ወረዳውን ከሌሎች አከባቢዎች የሚያገናኙ መንገዶች እንዲከፈቱና አስፈላጊው ሰብአዊ እርዳታ መድረሱን እንዲያረጋግጡ ኢሰመኮ በጥብቅ ያሳስባል።" ብሏል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን(ኢሰመኮ)።

ምንም አስተያየቶች የሉም