ዩኬ ለኢትዮጵያ እና ለሌሎች የቀጠናው አገራት የምትሰጠውን ድጋፍ በግማሽ ለመቀነስ መወሰኗ አስወቀሳት
የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ኢትዮጵያን ጨምሮ ለሌሎች የተመረጡ የአፍሪካ አገራት የሚያደርገውን የገንዘብ ድጎማ ለመቀነስ መወሰኑ አስወቀሰው።
የዩኬ ፓርላማ ኮሚቴ የአገሪቱ መንግሥት ለተወሰኑ የአፍሪካ አገራት የሚሰጠውን ድጎማ ለመቀነስ መወሰኑ "ግብዝነት ነው። እጅግም ያስቆጣል" ሲል ኮንኖታል።
ኢንተርናሽናል ዴቨሎፕመንት የተባለው ኮሚቴ፤ በተለይም በግጭት እየተናጡ ከሚገኙት የምሥራቅ አፍሪካ አገራት በግማሽ ወይም ከዚያም በላይ ድጎማ መቀነሱ አግባብ እንዳልሆነ አስታውቋል።
ይህ የዩኬ ፓርላማ ኮሚቴ አገሪቱ የምታደርጋቸው ልገሳዎች ላይ ትችት በመሰንዘር የሚታወቅ ሲሆን፤ ለኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሞዛምቢክ፣ ሶማሊያ እና ሌሎች የአፍሪካ አገራት የሚሰጠው ድጎማ መቀነሱ ተገቢ አይደለም ብሏል።
የዩኬ መንግሥት በበኩሉ ከአፍሪካ አገራት ድጎማ ለመቀነስ የወሰነው ኮሮናቫይረስ ባሳደረበት ተጽእኖ ምክንያት መሆኑን አስታውቋል።
ኮሚቴው ግን ሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ የሚገኙት አገራት ከመቼውም በላይ የዩኬን እርዳታ በሚፈልጉበት በዚህ ጊዜ ድጋፍ ለመቀነስ መወሰኑን ተችቷል።
እነዚህ የቀጠናው አገራት ከገቡበት የሰብአዊ ቀውስ ባሻገር የአየር ንብረት ለውጥ ካስከተለው ችግርም ጋር እየታገሉ በመሆኑ ድጎማ መቀነስ እንዳልነበረበት ኮሚቴው ገልጿል።
እነዚህ አገራት በዩኬ ድጎማ ከሚደረግላቸው አገራት መካከል ቅድሚያ የሚሰጣቸው (priority areas) መካከል ናቸው።
የዩኬ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተመረጡት የአፍሪካ አገራት ጋር "ብሔራዊ ጥቅምን ያማከለ ትስስር አለን" ቢልም ለአገራቱ የሚሰጠው ድጎማ በግማሽ ወይም ከዚያ በላይ እንደሚቀነስ ተገልጿል።
የኢንተርናሽናል ዴቨሎፕመንት ኮሚቴ ኃላፊዋ ሳራ ቻምፒዮን "ውሳኔው ግብዝ ነው። እጅግም ያስቆጣል። የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ቅድሚያ እንዲሰጣቸው የወጣውን የመንግሥት አቅጣጫ ይጻረራል" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ቀጠናው በከባድ ሰብአዊ ቀውስ፣ በግጭት፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና ለእድገት ማነቆ በሆኑ መሰናክሎች እየተፈተነ እንደሚገኝ ኃላፊዋ ጠቅሰዋል።
"በቀጠናው የውጭ ጉዳይ እና የደኅንነት ስትራቴጂን የከለሰው መንግሥት እነዚህን ችግሮች የሚቀንስ እርምጃ ይወስዳል ብለን ነበር" ሲሉም ውሳኔውን ተችተዋል።
ጨምረውም "ታዲያ ይሄ ውሳኔ እንዴት ነው ስትራቴጂ የሚያሳየው? እነዚህ አገራት ዩኬ ድጋፍ ከምታደርግላቸው አገራት ቅድሚያ የሚሰጣቸው መሆኑን እንዴት ነው የምናሳየው?" ብለዋል።
ዩኬ ከእነዚህ የአፍሪካ አገራት መካከል አንዳንዶቹን በደኅንት ጥበቃ ለመደገፍ ስትል ወታደሮቿ ስልጠና እንዲሰጡ እንደምትልክ ጠቅሰው፤ "ወታደሮች ስልጠና እንዲሰጧቸው ከላክን በኋላ ለልማት የሚያውሉትን ገንዘብ መቀነስ ትርጉም አይሰጥም" ሲሉ ተናግረዋል።
የፎሬን ዴቨሎፕመንት ኤንድ ኮመንዌልዝ ቢሮ መረጃ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ አምና ከዩኬ ያገኘችው 240.5 ሚሊዮን ፓውንድ ሲሆን ለዚህ ዓመት በእቅድ የተያዘው ደግሞ 107.6 ሚሊዮን ፓውንድ ነው።
ሱዳን አምና ያገኘችው 142.6 ሚሊዮን ፓውንድ፣ ለዘንድሮ የታቀደው 62.2 ሚሊዮን ፓውንድ ነው። ደቡብ ሱዳን ደግሞ አምና 135.3 ሚሊዮን ፓውንድ ተሰጥቷት፣ ለዚህ ዓመት 68.4 ሚሊዮን ፓውንድ ተመድቦላት ነበር።
ለሶማሊያ አምና የተለገሰው 121.1 ሚሊዮን ፓውንድ፣ ለዚህ ዓመት የታቀደው ደግሞ 71.2 ሚሊዮን ፓውንድ ሲሆን፤ ለኬንያ አምና የተሰጠው 67.3 ሚሊዮን ፓውንድ፣ ለዘንድሮ የታሰበው ደግሞ 41.0 ነበር።
ዩኬ እርዳታ ከቀነሰችባቸው አገሮች መካከል ኬንያ እና ሶማሊያ ውስጥ ወታደራዊ ስልጠና የምትሰጥባቸው ካምፖች አሏት። ሶማሊያ ውስጥ አክራሪነትን ለመዋጋትም ድጋፍ ታደርጋለች።
በልገሳ ዙርያ የሚሠሩ ባለሙያዎች እና ዲፕሎማቶች እንደሚሉት ለልማት የሚውል ድጎማ እና የደኅንነት ጉዳይ ጎን ለጎን ይሄዳሉ። ልማትን ለመደገፍ የሚሰጥ ድጎማ ደኅንነትን ከማስጠበቅ እና መረጋጋትን ከማረጋገጥ ጋር ይተሳሰራል ሲል ቢቢሲ አስነብቧል።

ምንም አስተያየቶች የሉም