Latest

ads header

ዜና

በበርሊን ማራቶን የፈጸምኩትን ስህተት አልደግምም - አትሌት ቀነኒሳ በቀለ

 

ቀነኒሳ በቀለ

አትሌት ቀነኒሳ በቀለ የፊታችን እሁድ በሚካሄደው የበርሊን ማራቶን ውድድር ላይ ከዚህ ቀደም በበርሊን ማራቶን የፈጸምኩትን ሰህተት አልደግምም አለ።

 

አትሌት ቀነኒሳ ከሁለት ዓመት በፊት እአአ 2019 ላይ በጀርመን መዲና በተካሄደው የማራቶን ውድድር የዓለም ክብረ ወሰንን ለመሻሻል ሁለት ሰኮንዶች ብቻ ቀርተዉት ውድድሩን ማሸነፉ ይታወሳል።

 

"ከውድድሩ በፊት ክብረ ወሰን ለማሻሻል አእምሮዬን አላዘጋጀሁም ነበር። ክብረ ወሰኑን ለመሻሻል አእምሮዬን ባዘጋጅ ኖሮ፤ ክብረ ወሰኑ የዚያን ዕለት ይሰበር ነበር" ሲል ቀነኒሳ ኢንስታግራም ገጹ ላይ ባጋራው ቪዲዮ ተናግሯል።

 

ቀነኒሳ በ2019ኙ የበርሊን ማራቶን ሁለት ሰከንዶች ብቻ ቀርተውት ክብረ ወሰን ሳያሻሽል መቅረቱ "ብዙ ጊዜ ያስደነግጠኛል" ያለ ሲሆን፤ እሁድ በሚደረገው ውድድር በኬንያዊው ኤሊዩድ ኪፕቾጌ የተያዘውን ሪኮርድ ለማሻሻል እቅድ እንዳለው ገልጿል።

 

ቀነኒሳ ባለፈው ዓመት በተካሄደው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ላይ በማራቶን ይሳተፋል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም ኢትዮጵያን የሚወክሉ ተወዳዳሪዎችን ለመምረጥ በተደረገው ማጣሪያ ላይ ባለመሳተፉ ከቡድኑ ውጪ መሆኑ ይታወቃል።

 

አትሌቱ 3 የኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ፣1 የኦሊምፒክ የብር ሜዳሊያ፣5 የዓለም ሻምፒዮን የወርቅ ሜዳሊያ እና 1 የዓለም ሻምፒዮን የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊ ነው፡፡

ቀነኒሳ ተመራጭ ከሚያደርጋቸው ውድድሮች መካከል የበርሊን ማራቶን አንዱ መሆኑን ይናገራል። "ብዙ ሰው የሚሳተፍበት ነው። ጥሩ የአየር ጸባይ ነው። ከተማውን እወደዋለሁ፤ ንፁህ ከተማ፤ ንፁህ አየር ነው ያለው" ብሏል።

 

ቀነኒሳ በአሁኑ ወቅት ለውድድሩ የመጨረሻ ዝግጅቱን ከአገር ውጪ እያደረገ እንደሆነም ተናግሯል።

 

በርሊን፣ ለንዶን፣ ቦስተን እና ኒው ዮርክ ከተሞች ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸውን የማራቶን ውድድሮችን ያዘጋጃሉ።

 

የበርሊን ማራቶን ደግሞ በተለየ መልኩ ብዙ ጊዜ ክብረ ወሰኖች የሚሻሻሉበት የውድድር መድረክ ሆኖ ቆይቷል።

 

በዘንድሮ ውድድር የማይሳተፈው ኢሉዩድ ኪፕቼጌ እአአ 2018 ላይ ተካሂዶ በነበረው የበርሊን ማራቶን 2፡01፡39 በሆነ ሰዓት የዓለም ክብረ ወሰንን ይዟል።

 

ቀነኒሳ ደግሞ ከአንድ ዓመት በኋላ፤ ማለትም እአአ 2019 ላይ 2፡01፡41 በሆነ ሰዓት መጨረስ ችሏል።

 

በበርሊን ማራቶን የተሻሻሉ ክብረ ወሰኖች

 

2:04:55 እአአ 2003 በኬንያዊው ፖል ቴርጋት

2:04:26 እአአ 2007 በኢትዮጵያዊው ኃይሌ ገ/ሥላሴ

2:03:59 እአአ 2008 በኢትዮጵያዊው ኃይሌ ገ/ሥላሴ

2:03:38 እአአ 2011 በኬንያዊው ፓርትሪክ ማካኡ

2፡03፡23 እአአ 2013 በኬንያዊው ዊልሰን ኪፕሳንጋ

2፡02፡57 እአአ 2014 በኬንያዊው ዴኒስ ኪሜቶ

2፡01፡39 እአአ 2018 በኬንያዊው ኢሉዩድ ኪፕቼጌ

በእሁዱ የበርሊን ማራቶን ሌሎች ተጠባቂ አትሌቶች

 

ከአትሌት ቀነኒሳ በቀለ በተጨማሪ፤ አስደናቂ ውጤት ማስመዝገብ የሚችሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተሳታፊ ይሆናሉ።

 

እአአ 2017 ላይ ኪፕቼጌን ተከትሎ ኢትዮጵያዊው ጉዬ አዶላ ሁለተኛ ሆኖ አጠናቋል። የ22 ዓመት ወጣት የሆነው ኦሊቃ አዱኛም በበርሊን ማራቶን ከሚጠበቁ አትሌቶች መካከል አንዱ ነው። ኦሊቃ እአአ 2020 ላይ የዱባይ ማራቶንን አሸንፏል።

 

እአአ 2021 ላይ በጃፓን የሚካሄደውን ሌክ ቢዋ ማራቶን ውድድርን ያሸነፈው ጃፓናዊው ሂዴካዙ ሂጂካታ ሌላኛው ተጠባቂ አትሌት ነው።

 

የበርሊን ማራቶን የወንዶች ውድድር እሁድ ጠዋት ይካሄዳል።

 

የሴቶች የማራቶን ውድድር

 

በሴቶች የበርሊን ማራቶን ውድድር የኢትዮጵያ እና ኬንያ አትሌቶች የአሸናፊነት ግምት ተሰጥቷቸዋል።

 

ሕይወት ገ/ኪዳን ሚላን ማራቶን ላይ ያስመዘገበችውን 2፡19፡25 ፈጣን ሰዓት ይዛ ውድድሩን ትጀምራለች።

 

የ2015 የኮፐንሃገን እና ሊዝበን ማራቶን ሻምፒዮኗ ኬንያዊቷ ፒዩሪቲ ሪኦኖሪፖ ሌላኛዋ ተጠባቂ አትሌት ነች።


ቢቢሲ


ምንም አስተያየቶች የሉም