የቀድሞው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር (አብዲ ኢሌ) በዐቃቤ ህግ የቀረበባቸውን ክስ እንዲከላከሉ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ብይን ሰጠ። ፍርድ ቤቱ ዛሬ ሰኞ ነሐሴ 22፤ 2015 በነበረው የችሎት ውሎ ከቀድሞው የክልል ርዕሰ መስተዳድር ጋር በአንድ መዝገብ ከተከሰሱ ግለሰቦች መካከል 16 ተከሰሾችን በነጻ ማሰናበቱን የአቶ አብዲ ጠበቃ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
የአቶ አብዲን ጉዳይ ሲመለከት የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የጸረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ችሎት፤ ለዛሬ ቀጠሮ ይዞ የነበረው ዐቃቤ ህግ ባቀረበው ክስ ላይ ብይን ለመስጠት ነበር። በዚህም መሰረት ጉዳያቸው በችሎቱ እየታየ ካሉት 42 ተከሳሾች ውስጥ 26 የሚሆኑት በዐቃቤ ህግ የቀረበባቸውን ክስ እንዲከላከሉ ፍርድ ቤቱ ብይን ሰጥቷል።
በዐቃቤ ህግ የቀረበባቸውን ክስ እንዲከላከሉ ከተባሉት ተከሳሾች መካከል፤ የሶማሌ ክልልን ለስምንት ዓመት ያስተዳደሩት አቶ አብዲ መሐመድ ይገኙበታል። “አብዲ ኢሌ” በሚለው ቅጽል ስማቸው የሚታወቁት የቀድሞው ርዕሰ መስተዳድር እንዲከላከሉ የተበየነባቸው፤ “የጦር መሳሪያ ይዞ በማመጽ፣ ወይም የእርስ በርስ ጦርነት በማስነሳት በመንግስት ላይ የሚደረግ ወንጀልን” ፈጽመዋል በሚል በዐቃቤ ህግ የቀረበባቸውን ዋና ክስ መሆኑን ጠበቃቸው መናገራቸውን ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘግቧል።
0 አስተያየቶች