አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከመጪው 2016 ዓ.ም. ጀምሮ የቅድመ ምረቃ ተማሪዎችን የሚቀበለው በምደባ ሳይሆን በውድድር መሆኑን አስታወቀ። ዩኒቨርስቲው ክፍያ የሚፈጽሙ የቅድመ ምረቃ ተማሪዎችን “በልዩ” ሁኔታ ለማስተማር እንዳቀደም ገልጿል።
አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ይህንን ያስታወቀው የመጀመሪያው ራስ ገዝ ዩኒቨርስቲ መሆኑን አስመልክቶ ዛሬ ማክሰኞ ነሐሴ 16፤ 2015 በዋናው ቅጥር ግቢ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው። መግለጫውን የሰጡት የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋሙ ራስ ገዝ ለመሆን ላለፉት ሁለት ዓመታት ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር ስር ያሉ የመንግስት ዩኒቨርስቲዎችን ራስ ገዝ ለማድረግ የተዘጋጀው አዋጅ በተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው ባለፈው ግንቦት ወር ነበር። የዚህን አዋጅ መውጣት ተከትሎም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያው ራስ ገዝ ዩኒቨርስቲ እንዲሆን ያስቻለው ደንብ፤ ከሶስት ሳምንት በፊት ሐምሌ 28፤ 2015 በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቋል።
የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት በዛሬው መግለጫቸው፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋሙ ወደ ራስ ገዝነት የሚያደርገውን ሽግግር “ሁለት ዓመት ባልሞላ” ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ማቀዱን አስታውቀዋል።
ምንጭ:- የኢትዮጵያ ኢንሳይደር
0 አስተያየቶች