For daily News Visite Agelgl Media
መኮና ሄጦሳ በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ሰባ ቡሩ ወረዳ ቡሳ ጎኖፋ የተሰኘ ድርጅት ኃላፊ ናቸው።
ቡሳ ጎኖፋ የተሰኘው ድርጅት በአደጋ መከላከል ላይ የሚሠራ መንግሥታዊ መዋቅር ነው።
አቶ መኮና በሰባ ቡሩ ወረዳ በተራዘመ ድርቅ ምክንያት 12 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
* Al-ShabaabFaces Pushback in Ethiopia’s Somali Region
በወረዳው ከሚገኙ ቀበሌዎች “በሰበሰብኩት መረጃ መሠረት የከፋ ድርቅ እየመጣ ነው” ይላሉ አቶ መኮና።
ኃላፊው ይህን ለማስረገጥ በቅርቡ አንዲት እናት ጡት እያጠባች ሕይወቷ ማለፉን በማስታወስ ይናገራሉ።
“ድሬ ሰባንሳ በተሰኘች ራቅ ብላ በምትገኝ ቀበሌ የምትኖር እናት ለቀናት ልጆቿን የምታበላው አጥታ ያገኘችውን ምግብ ለልጆች ሰጥታ ጋደም ባለችበት ሕይወቷ አልፏል። ጠዋት ልጇ የሙት እናቱን ጡት እየጠባ ነው የተገኘው።”
በወረዳው በድርቅ ምክንያት ሕይወታቸውን ካጡ መካከል አብዛኛዎቹ ሕፃናት መሆናቸውን ኃላፊው ይናገራሉ።
“አብዛኞቹ ሕፃናት ናቸው። አንድ ራሱን ያጠፋ አባወራም አለ። ‘እኔ እያለሁ ልጆቼ ከሚሞቱ’ በሚል ይመስላል ራሱን ያጠፋው።”
አቶ መኮና በአካባቢው የኦሮሞ ነፃነት ጦር እንቅስቃሴ ስለሚያደርግ ሰብዓዊ እርዳታ ማድረስ አዳጋች እንደሆነ ያስረዳሉ።
አክለውም በእርዳታ ሥራ ተሰማርተው የነበሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አካባቢውን ለቀው መውጣታቸው ችግሩን እንዳባባሰው ጠቅሰው “አፋጣኝ መፍትሔ ካልተገኘ ረሃብ ብዙ ሰው ሊፈጅ ይችላል” ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።
በአርባ ዓመታት ጊዜ ውስጥ ታይቶ አይታወቅም የተባለው ድርቅ በምሥራቅ አፍሪካ አገራት ሚሊዮኖች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ጠባቂ እንዲሆኑ አድርጓል።
ድርቁ በኦሮሚያ ክልል ባሉ 10 ዞኖች
3.7 ሚሊዮን ሰዎችን አደጋ ላይ ጥሏል ሲሉ የኦሮሚያ ቡሳ ጎኖፋ ኃላፊ ሙስጠፋ ኸድር ተናግረዋል።
ነገር ግን ኃላፊው በተለያዩ ወረዳዎች ከሚገኙ የመሥሪያ ቤታቸው ኃላፊዎች በተቃራኒ “በረሃብ የሞተ ሰው የለም” ይላሉ።
“አሁን ባለው ሁኔታ ረሃብ ተብሎ ሊታወጅ የሚችል አይደለም። በረሃብ ምክንያት ኦሮሚያ ውስጥ የሞተ ሰው የለም።”
“በሰባ ቦሩ ስታጠባ የነበረች እናት ሞታ መገኘቷ እውነት ነው። ነገር ግን በረሃብ ስለመሞቷ መረጃ አልተገኘም። ቤቷ እህል ነበር። የሞቷን ምክንያት እያጣራን ነው።”
በተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም (ደብሊው ኤፍ ፒ) ባለፈው ወር መጀመሪያ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ድርቅ በማስመልከት ባወጣው ዘገባ እስከ ሚያዝያ ባለው ጊዜ በድርቅ ምክንያት በአገሪቱ 7.2 ሚሊዮን ሰዎች የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ብሏል።
ድርጅቱ ባለፈው ጥር ኢትዮጵያ ውስጥ በድርቅ የተጎዱ ሰዎች ቁጥር 5.7 ሚሊዮን ነው ማለቱ ይታወሳሉ።
የመንግሥታቱ ድርጅት ተቋም ይህን መረጃ ባለፈው ጥር ካወጣ በኋላ ተጨማሪ 1.5 ሚሊዮን ሰዎች በድርቅ ተጎድተዋል።
ከክልሉ ኃላፊዎች እንደሰማነው በኦሮሚያ ክልል ብቻ የድርቅ ተጎጂዎች ቁጥር 3.7 ሚሊዮን ደርሷል።
በቅርብ ጊዜ የኢትዮጵያ ታሪክ ‘ታይቶ አይታወቅም’ በተባለው ድርቅ በደቡብና ደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ አርብቶ አደርና ከፊል አርብ አደሮችን እየጎዳ መሆኑን የዓለም ምግብ ፕሮግራም ገልጧል።
በሌላ በኩል በቅርቡ በደቡብ ክልል ኮንሶ ዞን በምግብ እጥረት ሳቢያ 13 ሕፃናት ሕይወታቸው ማለፉት የአካባቢው ባለሥልጣናት ለቢቢሲ መናገራቸው ይታወሳል።
በአማራ ክልል በዋግ ኽምራ ዞንም እንዲሁ በተመሳሳይ በድርቅ ምክንያት ሕዝቡ ለከፍተኛ ችግር መጋለጡን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም እየጨመረ ያለውን የተጎጂዎች ቁጥር ከግምት በማስገባት ሁሉንም ለመድረስ የገንዘብ እጥረት ማጋጠሙን ገልጧል።
ድርጅቱ እስካሁን በቁጥር የተለዩትን 7.2 ሚሊዮን ሰዎች በአግባቡ ለመደገፍ 343 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው አሳውቋል።
ድርቅ እና ፖለቲካ
ኢትዮጵያ ውስጥ የከፋ ድርቅ ሊከሰት እንደሚችል ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አስቀድመው ቢገምቱም በሰሜንና በደቡብ አቅጣጫዎች ከታጣቂዎች ጋር ጦርነት ውስጥ የገባው መንግሥት ይህን ችግር ለመጋፈጥ ፈተና የገጠመው ይመስላል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ጦርነት ተከትሎ ‘መንግሥት ረሃብን እንደ ጦርነት መሣሪያ እየተጠቀመ ነው’ የሚሉ ወቀሳዎች ከዓለም አቀፍ ተቋማት ሲደመጡ ነበር።
የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ይህን ወቀሳ አጥብቆ እንደሚያወግዝ በተደጋጋሚ ገልጧል።
በግጭት ምክንያት ለድርቅ የተጋለጡ ነዋሪዎችን ጨምሮ በዝናብ እጥረት ምክንያት በተከሰተ ድርቅ ሚሊዮኖች እርዳታ እየጠበቁ ይገኛሉ።
በኦሮሚያ ክልል በቅርቡ የተከሰተውን የተመለከቱ፤ ጉዳዩ ለፖለቲካ ዓላማ እየዋለ ነው ብለው ትችት ይሰነዝራሉ።
የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ኃላፊዎችን በመተቸት የሚታወቁት የሰላም ሚኒስቴር ዲኤታ አቶ ታዬ ደንደአ፤ በጉጂ ዞን ሊበን ወረዳ በረሃብ ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡ ናቸው ያሏቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር በማኅበራዊ ሚድያ ገፆቻቸው ላይ አስፍረዋል።
ሚኒስትር ዲኤታው አክለውም “ሕዝባችን የከፋ ችግር ውስጥ ነው። በጣም የከፋው ደግሞ የችግሩን መጠን መደበቃችን ነው. . . በኦሮሚያ ክልል ምን ያህል ሰው በድርቅና በረሃብ እንደተፈናቀለ አይታወቅም” ሲሉ ጽፈዋል።
አቶ ታዬ ይህን መልዕክት በለጠፉ በሰዓታት ጊዜ ውስጥ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ (ኦቢኤን) ሚኒስትሩ ወዳሉት ሥፍራ በማቅናት ‘በረሃብ የሞተ የለም’ የሚል ዘገባ አስተላልፏል።
በረሃብ ሞተዋል የተባሉ ሰዎችም ገሚሶቹ በሌላ ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡ፣ ሌሎቹ ደግሞ በሕይወት ያሉ ናቸው ሲል የጉጂ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ኡዶን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
የኦሮምያ ቡሳ ጎኖፋ ኃላፊ መስጠፋ ከድር በበኩላቸው ይህን ይላሉ።
“ባለፈው ዓመት አልደበቅንም፤ አሁንም አንደብቅም። ሆነ ብለው ለፖለቲካ ጥቅማቸው ጉዳዩን የሚጠቀሙበት ሰዎች አሉ። ግን የሞተ ሰው የለም። ውሸት ነው። የድርቁ ጉዳት አሁን ከመንግሥት አቅም በላይ አልሆነም።”
ነገር ግን እስካሁን ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ በመጪው መስከረም እና ጥቅምት የከፋ አደጋ ሊደርስ እንደሚችል ኃላፊው ይናገራሉ።
ነገር ግን መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት እየተሰማ ያለው መረጃ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ሌሎችም የምሥራቅ አፍሪካ አገራትም የድርቅ አደጋው እንደተደቀነባቸው ያሳያል።
የተባበሩት መንግሥት የስተደኞች ተቋም በምግብ ዋጋ መወደድና በከፍተኛ ድርቅ ምክንያት የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ለረሃብ ሊጋለጡ ይችላሉ ይላል።
ተቋሙ እንደሚለው በሶማሊያ፣ በኬንያና በኢትዮጵያ በግብርና እና በከብት እርባታ የሚተዳደሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነዋሪዎች የድርቅ አደጋ አንዣቦባቸዋል።
ባለፈው የካቲትም ዩኒሴፍ የተሰኘው የተባበሩት መንግሥታት ተቋም በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብና በሶማሌ ክልሎች ሚሊዮኖች በድርቅ ምክንያት ለችግር ተጋልጠዋል ብሎ ነበር።
ድርጅቱ በአራት አሥርት ዓመታት ታይቶ አይታወቅም በተባለው ድርቅ ምክንያት በርካታ ሚሊዮኖች እርዳታ ጠባቂ ይሆናሉ ብሎ ገምቶ ነበር።
የተባበሩት መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ዩኤንኦቻ) ላለፉት ሰባት ዓመታት ማለትም ከፈረንጆቹ 2015-22 ድረስ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ድርቅ የተመለከተ ዘገባ አውጥቷል።
በ2015/16 ኤል ኒኖ የተሰኘ የተፈጥሮ አደጋ ተከትሎ የተከሰተው ድርቅ በደቡብና ደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥፋት አስከትሏል።
ይህ የተፈጥሮ አደጋ ባስከተለው ድርቅ በዝቅተኛ አካባቢዎች የሚኖሩ አርብቶ አደሮች ሰብዓዊ እርዳታ ለመጠበቅ ተገደው ነበር።
በዚህ ድርቅ ሳቢያ በቀጣዩ በፈረንጆቹ 2017፤ 5.6 ሚሊዮን ሰዎች የምግብ እርዳታ፣ 2.9 ሚሊዮን ሕፃናት እና እናቶች ደግሞ ተጨማሪ ምግብ፣ 9.2 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ንጹህ ውሃ አስፈልጓቸው ነበር።
ብዙውን ጊዜ በኢትዮጵያ የድርቅ አደጋ የሚከሰተው ከታኅሣሥ እስከ መጋቢት ባለው ጊዜ ነው። ይህ ድርቅ በግብርና ምርትና በከብት እርባታ የሚተዳደሩ ነዋሪዎችን ያጠቃል።
ከ2015-17 ባሉት ሦስት ዓመታት በደቡባዊ ኢትዮጵያ የተጠበቀውን ያህል ዝናብ ባለመጣሉ 8.5 ሚሊዮን ሰዎች እርዳታ ጠባቂዎች ነበሩ።
የመንግሥት
ዝግጁነት
ኢትዮጵያ
ውስጥ ሚሊዮኖች የምግብ እርዳታ ጠባቂ እንዲሆኑ ያደረገው ተፈጥራዊ አደጋ ብቻ አይደለም።
ከትግራይ
ተነስቶ ወደ አጎራባች የአማራና የአፋር ክልሎች የተስፋፋው የሰሜኑ ጦርነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቅለው ሰብዓዊ
እርዳታ እንዲጠብቁ አስገድዷቸዋል።
አልፎም
በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት መሠረት ልማቶች መውደማቸውን ተከትሎ እርዳታ ማድረስ
አስቸጋሪ እንደሆነባቸው ሰብዓዊ እርዳታ አድራሽ ድርጅቶች ይገልጣሉ።
የተባበሩት
መንግሥታት መረጃ እንደሚያሳየው ተፈጥራዊና ሰው ሠራሽ በሆኑ ምክንያቶች 20 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች እርዳታ ይሻሉ።
ድርቅ
በለጸጉ በሚባሉ እንደ አሜሪካና የአውሮፓ አገራት የሚከሰት ቢሆንም የኢትዮጵያ መንግሥት ድርቅን የመቋቋም አቅም ደካማ ነው የሚሉት
የፔልም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ኃይለ አርአያ (ዶ/ር) ናቸው።
ባለሙያው
በተለያዩ ምክንያቶች ሳቢያ መንግሥት እና ሕዝብ ይህንን አደጋ ቀድሞ ለመካለከል ያደረገው ዝግጁነት በቂ አይደለም ይላሉ።
አልፎም
አብዛኛው ሕብረተሰብ የአየር ሁኔታ ትንበያን ተከታትሎ ቀድሞ የመዘጋጀት ባሕል ስለሌለው ችግሩ ተባብሷል ባይ ናቸው።
ኃይለ
እንደሚሉት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የምግብ ዋጋ መናር እና የምጣኔ ሃብት ችግር ተጨማሪ ጫና ፈጥረዋል።
“ሕዝቡ
ይህን አደጋ የመቋቋም አቅሙ ደካማ ነው ማለት ሕብረተሰቡ የሚያመርተውና የሚያከማቸው ምርት አነስተኛ ነው ማለት ነው። ከመኸር በፊትና
በኋላ ደግሞ የምርት አያያዝ ችግር ይታያል። መንግሥት ደግሞ ይህን ለመሸፈን አቅሙ ዉሱን ነው” ይላሉ።
አርሶ
አደሩ ኅብረተሰብ ግብርናው በዝናብ ላይ የተመሰረተ ከመሆኑ በተጨማሪ መንግሥትና ምሁራን ይህንን ለመቀልበስ ብዙ ሥራ አልተሠራም
የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ በአገሪቱ ውስጥ ያለው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ደግሞ እርዳታ ወደሚያስፈልጋቸው ቦታዎች በነፃነት መጓዝ እንዳይችል
እንቅፋት መሆኑን አመልክተዋል።
አክለውም
እንዲህ አይነቱን ተደጋጋሚ የድርቅ ክስተት ለመቋቋም መንግሥት ለሰፋፊ እርሻዎች የሰጠውን ትኩረት ለአነስተኛ እርሻዎች መስጠት አለበት።
“ገበሬው
ለገበያ የሚተርፍ ምርት ማምረት አይችልም እየተባለ የሚነገረው አርሶ አደሩን የገበያ ዋስትና እንዲያጣ ያደርገዋል። ለዚህ ነው ድርቅ
ሲከሰት ለከፋ ችግር የሚጋለጠው።”
በድርቅ
የተጠቁ አካባቢዎችን መድረስ አዳጋች መሆን፣ የመንገድ ደኅንነት ዋስትና አለመኖር፣ የገበያ ትስስር አለመፈጠሩ በድርቅ ምክንያት
ከፍተኛ አደጋ ውስጥ የሚወድቀው ሕብረተሰብ ቁጥር እንዲሁም የእንስሳት ሞት እንዲጨምር አድርጓል ይላሉ።
“እኛ
አገር ድርቅ ሳይታሰብ ተከሰተ ነው የሚባለው፤ ሌሎች አገሮች ግን ይዘጋጁበታል። እኛ ጋር ዝግጁነት የለም” የሚሉት ባሙያው እንደመፍትሔ
የሚያስቀምጡት አስቀድሞ መዘጋጀትን ነው።
አልፎም
ለአርብቶ እና አርሶ አደሮች የሚሆን ፕሮጀክት ሊቀረጽ እና አማራጭ የውሃ አቅርቦት (የውሃ ባንክ) ሊኖር እንደሚገባ ያሰምራሉ።
የኢትዮጵያ
አደጋ ስጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን በበኩሉ መንግሥት ድርቁን ለመቋቋም በቂ ዝግጅት አላደረገም የሚለውን ትችት አይቀበለውም።
ኮሚሽኑ
በድርቅ ምክንያት ለተጎዱ አካባቢዎች መንግሥት እርዳታ እያቀረበ ነው ይላል።
ኮሚሽኑ፤
በሶማሌ ክልል 9 ዞኖች በድርቅ መጎዳታቸውን እና በዚህ ምክንያት ከብቶች መሞታቸውን ይገልጻል።
በተመሳሳይ
ደቡብ እና ኦሮሚያ ክልሎች በድርቅ መጎዳታቸውን አምኖ መንግሥት አስፈላጊውን እርዳታ እያቀረበ ነው ይላል።
ከ2013-14
ባለው በሦስቱ ክልሎች በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች የምግብ እና ገንዘብ እርዳታ እንዲደርሳቸው ተደርጓል ይላሉ የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት
ዳይሬክተር ደበበ ዘውዴ።
ዳይሬክተሩ
እንደሚሉት በኦሮሚያ ክልል ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር 3.2 ሚሊዮን ደርሷል። ከእነዚህ መካከል ለተወሰኑት ከአንድ ሚሊዮን
ኩንታል በላይ የምግብ እርዳታ ቀርቧል።
ጨምረውም
“ከአንድ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ከዓለም ባንክ የተገኘ 900 ሚሊዮን ብር ተሰራጭቷል” ብለዋል።
በሶማሌ
ክልልም እንዲሁ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ኩንታል የምግብ እርዳታ እንደተሰራጨ ዳይሬክተሩ ለቢቢሲ ገልጸው፣ ይህም ለአንድ ወር የሚሆን
የምግብ እርዳታ እንደሆነና “ይህንንም አብቃቅቶ መጠቀም የክልሎች ኃላፊነት ነው” ሲሉ ጠቅሰዋል።
በተመሳሳይ
በደቡብ ክልል ለ106 ሺህ የምግብ እርዳታ ፈላጊዎች 39 ሺህ ኩንታል ድጋፍ ተደርጓል የሚሉት ኃላፊው፣ ከዓለም ባንክ የተገኘ
498 ሚሊዮን ብር እስከ ግንቦት ወር ድረስ ድጋፍ ተደርጓል ሲሉ ያክላሉ።
“መንግሥት
ስለተዘጋጀ ነው ይህን ድጋፍ እያደረገ ያለው። ድርቁ በዝናብ እጥረት ምክንያት የመጣ ነው። የአየር ጠባይ ለውጥ ያመጣው ተፅዕኖ
ነው። ቢሆንም ጫናውን ለመቋቋም ከፍተኛ ጥረት አድርገናል። እርዳታው በቂ ላይሆን ይችላል ነገር ግን መንግሥት እርዳታ በሚያስፈልግበት
ሁሉ ድጋፍ እያደረገ ነው።”
የሕዝብ
ግንኙነት ኃላፊው በአንዳንድ ቦታዎች እንደሚባለው በድርቅ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ስለመኖራቸው ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት
ተቆጥበዋል።
ምንጭ፡- ቢቢሲ
0 አስተያየቶች