ሁለት የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች በአዲሱ የአማራ ክልል ም/ቤት ተሾሙ
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ(አብን) እና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄ(አዴሃን) አመራሮች በአዲሱ የአማራ ክልል ካቢኔ ውስጥ ተካተው በዛሬው እለት (መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም) ተሾመዋል።
ሰኔ 14፣ 2013 ዓ.ም በተካሄደው ሀገራዊ ምርጫ በአማራ ክልል አብላጫ ድምጽ ያገኘው፣ የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ዛሬ ክልሉን ለቀጣይ አምስት መታት የሚመራ አዲስ መንግሥት መስርቷል።
በክልሉ ሹመት ያገኙት የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች አቶ ጣሂር መሀመድ ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እና አቶ ተስፋሁን አለምነህ ከአዴሃን ናቸው።
የአብን የህዝብ ግኝኑት ኃላፊ አቶ ጣሂር ሙሃመድ የክልሉ የቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ፤ የአዴሃኑ አቶ ተስፋሁን አለምነህ ደግሞ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ሆነው ተሾመዋል።
አዲሱ የክልሉ ምክር ቤት፤ የአማራ ክልል ትምህርት ቤሮ ኃለፊ ሆነው ሲያገለግሉ የነሩትን ይልቃል ከፋለን(ዶ/ር) የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አድርጎ በመሾም ቃለ መሃላ አስፈፅሟል።
ክልሉን ለመምራት ስልጣን ከቀደሞው ርእስ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር የተረከቡት ይልቃል ከፋለ(ዶ/ር) በክልሉ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ቃል ገብተዋል።
አዲስ የተመሰረተው የአዲስ አበባ ከተማ መንግስትም ለሁለት የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ሹመት መስጠቱ የሚታወስ ሲሆን፤ በዚህም የአብኑ የሱፍ ኢብራሂም የንብረት አስተዳደር ባለስለጣን፤ የኢዜማው አቶ ግርማ ሰይፉ ደግሞ የኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ በመሆን ተሾመዋል።
ነገርግን አቶ የሱፍም ሆነ፤ አቶ ግርማ ሰይፍ በሹመቱ ዙሪያ ያሉት ነገር የለም።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር ከአል ዐይን አማርኛ ጋር በቅርቡ በነበራቸው ቆይታ በአዲሱ የፌደራል መንግስት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ወኪሎች ሃሳባቸውን ለሕዝብ የሚያቀርቡበት፤ በተለያዩ የመንግስት እርከኖች ውስጥ የሚሳተፉበት እድል እንደሚኖር መናገራቸው ይታወሳል።
በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ፤ ብልጽግና ፓርቲ አብላጫ ድምጽ ማግኘቱንና ሌሎች ሶስት ተቀዋሚ ፖርቲዎች የፓርላ መቀመጫ ማሸነፋቸውን ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ማስታወቁ ይታወሳል።
ጠቅላላ ምርጫው በተለያየ ምክንያት በሁሉም የምርጫ ክልሎች መካሄድ ባይችልም፣ ምርጫ ቦርድ መንግስት ለመመስረት የሚያስችል ድምጽ መገኘቱን ይፋ አድርጎ ነበር።
የህዝብ ተወካዮች ም/ቤትም መስከረም 24 አዲስ መንግስት እንደሚመሰረት አስታውቋል።
ምንም አስተያየቶች የሉም