Ticker

6/recent/ticker-posts

ከመቐለ - አዲስ አበባ - ዩክሬን፡ አስደናቂው የትዕግስት ጉዞ



"በእግራችን 30 ኪሎ ሜትር ተጉዘናል፤ ድንበር ላይ ለ14 ሰዓታት ቆመናል፤ ጥይት እንደ ቆሎ ሲንጣጣ ሰምተናል፤ ተዋጊ አውሮፕላኖች እያፏጩ ሲያልፉ ተመልክተናል፣ ዘረኝነት አይኑን አፍጥጦብናል።" 


ይህ የትዕግስት ታሪክ ነው። 


ትዕግስት [ለዚህ ታሪክ ሲባል ስሟ የተቀየረ] ዓለማችን ባለፉት ሁለት ዓመታት ካየቻቸው ጦርነቶች አበይቱን አይታለች። በትግራይና በዩክሬን። 


ትዕግስት ወደ ዩክሬን ያቀናችው ከአምስት ወራት በፊት ነበር። በትምህርት ቪዛ ኪዬቭ ብትገባም ዓላማዋ ዩክሬንን እንደመሸጋገሪያ መጠቀም ነበር። 


ነገር ግን ብዙም ሳትቆይ ሩሲያ የጦርነት ነጋሪት ትጎስም ጀመር። ለነገሩ ሩሲያ ዩክሬንን ልትወር ነው የሚለው ዜና ለዩክሬናዊያን ብርቃቸው አይደለም። 


"እኔ እዛ ከደረስኩ በኋላም ይህ ዜና ይሰማ ነበር። ነገር ግን እነርሱ [ዩክሬናዊያን] ምንም አይመስላቸውም። ክራይሚያ የሚባለው ቦታ አልፎ አልፎ ጦርነት ስላለ የተለመደ ነገር ነው" ትላለች ትዕግስት። 


አዲስ አበባ 


ትዕግስት ወደ ዩክሬን ከማቅናቷ በፊት ኑሯዋ አዲስ አበባ ነበር። "ወጣ ገባ ያለ ሥራ እየሠራሁ ነበር ኑሮዬን የምገፋው" ትላለች። 


ቤተሰቦቿ ደግሞ የከተሙት መቀለ ነው። 


ነገር ግን የትግራይ ጦርነት ሲቀሰቀስ እንደ ቀድሞው በነፃነት ተመላልሳ ቤተሰቦቿን መጎብኘት ይቅርና በስልክ መስመር እንኳ ልታገኛቸው አልቻለችም። 


"አዲስ አበባ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር አንዲት አነስ ያለች ምግብ ቤት ከፍተን እንሠራ ነበር። ነገር ግን አከራያችን ትግርኛ ተናጋሪዎች ስለሆናችሁ እኔ ላይ መዘዝ ታመጡብኛላችሁ ብሎ ስጋት ያዘው። ይኼኔ ነው ሥራውን ለማቋረጥ የወስንነው።" 


የመንግሥት ኃይሎች መቀለን ተቆጣጥረው አንፃራዊ መረጋጋት ሰፍኖ ትራንስፖርት ግልጋሎት መስጠት ከጀመረ በኋላ ነው የቤተሰቦቿን ድምፅ በቀጭኑ ሽቦ የሰማችው። 


መቐለ 


ወርሃ ግንቦት ላይ ከወደ መቀለ የመጣው የስልክ መልዕክት የሐዘን ዜና የታከለበት ነበር። ትዕግስት ከታናሽ እህቷ ጋር የቤተሰብ ሐዘንን ለመድረስ ወደ መቀለ በረሩ። 


"ትዝ ይለኛል ወደ መቀለ ስመለስ ሁኔታዎች እጅግ ተቀያይረው ነበር። አጋጣሚ ሆኖ ዶ/ር አብርሃም [በወቅቱ የጊዜያዊው አስተዳደር ኃላፊ] እኛ የነበርንበት አውሮፕላን ውስጥ ስለነበሩ ጠባቂዎቹ አውሮፕላኑን ከበውት ነበር። ከተማዋ በወታደር ተከብባ፤ ዝምታ ሰፍኖባት ማየት ያው ትንሽ ያስከፋል።" 


"ከዚያ በፊት አየር መንገድ ስትደርስ ታክሲ እንደልብ ታገኛለህ። ወታደር ብዙ አታይም። ብቻ በጣም ያስፈራ ነበር።" 


ትዕግስት መቀለ ደርሳ አባቷን በአካል በማግኘቷ የተሰማት ደስታ ጥልቅ ነበር። 


"አባቴ ስላሳለፈው ጊዜ ብዙ ማውራት አልፈልግም፤ ቢሆንም ከባድ ጊዜ እንዳሳለፈ ሲያጫውተኝ ነበር።" 


ትዕግስት ለቅሶ ደርሳ፤ አባቷን ጠይቃ፤ ወዳጅ ዘመዶቿን አግኝታ ወደ አዲስ አበባ በተመለሰች በሳምንቱ የትግራይ ኃይሎች መቀለን ተቆጣጠሩ። 


መንገድ ድጋሚ ተዘጋ፤ የስልክ ግንኙነት መስመርም ተቋረጠ። 


ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰች በኋላ ወደ ውጭ ለመውጣት አማራጮች ማፈላለግ ጀመረች። ይሄኔ ነው የዩክሬን ሐሳብ የመጣው።




ዩክሬን ለምን? 


ትዕግስት ዩክሬን ለመሄድ የወሰንኩት ሂደቱ ቀላል ነው የሚል መረጃ ስላገኘሁ ነው ትላለች። 


"ጓደኛዬ ዩክሬን ብንሄድ ቪዛው ብዙ ላይከብደን ይችላል፤ የትምህርት ቤት ክፍያውም እንደሌሎቹ አይከብደንም ትለኝ ነበርና አብረን ማሰላሰል ያዝን። በወቅቱ ብዙ ሰው ዩክሬንን እንደ መሸጋገሪያ ለመጠቀም ያመለክት ነበር። 


"እኔ ዕድለኛ ሆኜ ያለኤጀንት [ወኪል] ነው ማመልከቻ ያስገባሁት። በኤጀንት በኩል እንደሚያመልክቱ ሰዎች ያህልም ወጭ አላወጣሁም። መጀመሪያ አልተሳካልኝም ነበር። ነገር ግን በሁለተኛው ዙር ተሳካልኝ።" 


ትዕግስት ሁሉም ሰምሮላት ባለፈው ጥቅምት ወደ ኪዬቭ አቀናች። 


ኪዬቭ 


ትዕግስት በፈገግታ ታጅባ የዩክሬን መዲና ኪዬቭ ስትደርስ ከባድ ብርድ እንደተቀበላት ትናገራለች። 


"ቋንቋም በጣም አስቸጋሪ ነው። ነገር ግን እኔ ኪዬቭ ስለነበርኩ በአንፃራዊነት እንግሊዝኛ ተናጋሪ ይበዛል። ጓደኛዬ ቀድማ ደርሳ ስለነበር ቤት ተከራይታ፤ ሁሉን ነገር አመቻችታ ነበር የጠበቀችኝ 


"ዩክሬን ለመቆየት ሕጋዊ ወረቀት ሊኖኝ ይገባ ስለነበር ወደ ትምህርት ቤት ሄጄ፤ የአንድ ዓመት ክፍያ ከፍዬ፤ ማመልከቻዬን አስገባሁ። ፈቃድም አገኘሁ። ለቋንቋ ትምህርት ከሆነ የአንድ ዓመት የመኖሪያ ፈቃድ ይሰጣሉ። ለድግሪ ትምህርት ከሆነ ደግሞ የአራት ዓመት መኖሪያ ፈቃድ ይገኛል።" 


ትዕግስት ዩክሬንን እንደ መሸጋሪያ ተጠቅማ፤ አንድም ሁለትም ዓመት ቆይታ ወደ አሜሪካ የማቅናት የረዥም ጊዜ ዕቅድ እንደነበራት ታወሳለች። 


"ዩክሬን ከገባሁ በኋላ ሐሳቤን ቀይሬ ወደ አንድ የአውሮፓ አገር ቪዛ (ሸንገን) ለማቅናት ወሰንኩ።" 


የጦርነት ወሬ 


ትዕግስት ኪዬቭ ከገባችበት ጊዜ ጀምሮ ሩሲያ ዩክሬንን ልትወር ይሆን የሚለው ጥያቄ ተደጋግሞ ይነሳ ነበር። 


"እርግጥ ነው እኔ ከሄድኩ ብዙ ጊዜ አልሆነኝም። ነገር ግን ክራይሚያ በምትባለው ሥፍራ ቀዝቀዝ ያለ ጦርነት ሁሌም እንዳለ ነበር የምንሰማው። ሥራ ላይ ሳለሁ ዩክሬናዊያንን እጠይቅ ነበርና 'አይ ዛቻ ብቻ ነው፤ ሁሌም የምንሰማው ነው' ይሉኝ ነበር።"


ሥራ ጀምረሽ ነበር እንዴ?" 


"እርግጥ ለትምህርት መጥተን ሥራ እንድሠራ አይፈቀድልንም ነበር። ነገር ግን በርካታ ተማሪዎች ራሳቸውን ለመደጎም የተለያዩ ሥራዎች ይሠራሉ። በተለይ እንግሊዝኛ የሚናገሩ ይፈለጋሉ። እኔም 'ከስተመር ሰፖርት' እሠራ ነበር። 
"ከዚያ ባለፈው ወር ልክ እንደ ኳስ ግጥሚያ ቀን ይቆረጥለት ጀመር። [በእነርሱ አቆጣጠር ] ፌብሩዋሪ 15 ነው ይሉናል፤ አይደለም 16 ነው ይሉናል። በዚያ ቀን ከቤት እንዳትወጡ፤ ሥራም እንዳትመጡ የሚል መልዕክት ይደርሰን ጀመር።" 

የወረራ ቀን 

ረቡዕ የካቲት 17/2014 ዓ.ም ንጋት ሩሲያ በይፋ ዩክሬንን ወረረች። ዓለም ጆሮውን ቀስሮ የሚሆነውን መከታተል ያዘ። የሩሲያ ጦር በሰዓታት አሊያም በጥቂት ቀናት ኪዬቭን ይቆጣጠራል ተባለ። 
በዚህ ቀን ትዕግስት ጓደኞቿ አልጋቸው ላይ ነበሩ። ድንገት ቴሌግራም ላይ ከቤት አትውጡ የሚል መልዕክት ይደርሳቸው ጀመር። ግማሹ ደግሞ ፍንዳታ ሰምቻለሁ እያለ ይፅፍ ገባ። በደቂቃዎች ውስጥ ሁሉም ነገር ተደበላለቀ። 
"ንጋት 12 ሰዓት አካባቢ ነው። ከሥራ ቦታ 'አትምጡ' የሚል መልዕክት ደረሰን። የተኩስ ድምፅ እንሰማ ጀመር። ኪዬቭ ትጠቃለች ይባል ስለነበር ለመውጣት ወሰንን። ሦስት አራት ሰዓት አካባቢ ወጥተን ጓደኞቻችን ለመቀላቀል ነበር ዓላማችን። 
"ከኛ መኖሪያ ቤት ተነስቶ ወደ ዋና ከተማዋ ለመሄድ አንድ ወንዝ ማቋረጥ ነበረብን። ወንዙን የምንሻገርበት ድልድይ ሊመታ ይችላል ብለን በጣም ሰግተን ነበር።"
ትዕግስት ወደከተማ ሲወጡ ባንክ በጣም ከባድ ሰልፍ እንደነበር፤ ሱፐርማርኬትም እንዲሁ በጣም ረዥም ሰልፍ እንደሞላው፤ ትራንስፖርት ማግኘት የማይታሰብ እንደሆነ፤ መንገዱ በጣም ተጨናንቆ እንደነበር፤ ባቡር ጣቢያው በሰው እንደታጨቀ ታስታውሳለች።
"ከዚያ በፊት 500 ከፍለን [በዩክሬን መገበያያ ገንዘብ] የምንጓዝበት መንገድ እስከ 5ሺህ እና 6 ሺህ ደርሶ ነበር።"
ትዕግስትና የቅርብ ጓደኛዋ ሌሎች የምዕራብ አፍሪካ ወዳጆቻቸውን ተቀላቅለው የመጀመሪያውን ምሽት እዚያው ኪዬቭ አሳለፉ።


በቀጣዩ ቀን ኪዬቭ በጥይት ድምፅና በአየር ጥቃት ተናጠች። ጥቃት ሲኖር የሚሰማ የነብስ አድን ጥሪ ከተማዋ ላይ ከተሰቀሉ ድምፅ ማጉያዎች ይሰማ ጀመር።
"ድንገት ከተማ እያለን ይሄን 'ሳይረን' ሰማን። በቃ ሩጫ ነው። እግሬ አውጪኝ ነው። ጥቃቱ ከየት እንደሚመጣ አታውቅም። በሰማይ ጄቶች እያፏጩ ያልፋሉ። ከርቀት የተኩስ ድምፅ እንሰማለን። ሁሉም ሰው ከጥቃቱ ለመሸሽ ከምድር በታች ወዳለ ባቡር ጣቢያ ገባ። እኛም ተከትለን ገባን።"


ትዕግስትና ሁለተኛውንም ቀን እንዲሁ በጋራ ካሳለፉ በኋላ ወደ ልቭይቭ ከተማ ለማቅናት ወሰኑ። ከተማዋ ለፖላንድ ድንበር ቅርበት አላት። ዓላማቸው ወደ ድንበር አቅንተው ፖላንድ መግባት ነበር።


"እንኳን እኛ የአገሩ ዜጋ ነቅሎ እየወጣ ነበር። በረራ እንደታገደ እናውቃለን። ስለዚህ በመኪና ይሁን በባቡር አሊያም በእግር ያለንን አማራጭ ተጠቅመን መውጣት አለብን።

ጉዞ ወደ ልቭይቭ


ትዕግስትና ሌሎች ሰባት ጓደኞቿ በአጠቃላይ ስምንት ሆነው ከረዥም ጊዜ ጥበቃ በኋላ ወደ ልቭይቭ የሚወስዷቸው መኪና ተከራዩ።
"ስምንት ስለነበር አራት ሰው በአንድ መኪና፤ ሌሎቻችን ደግሞ በሌላ መኪና መሆን ነበረብን። ለወትሮው 7 አሊያም 8 ሰዓት የሚወስደውን መንገድ በ24 ሰዓታት ነው የጨረስነው። በጣም ከባድ የትራፊክ መጨናነቅ ነበር። መንገድ ላይ ታንኮች ተደርድረዋል። መድፍ ይታያል። ወታደሮች ታጥቀው ይዞራሉ።"
እነ ትግዕስት ይህንን ሁሉ ተጉዘውም ወደ መሻገሪያ ድንበር አልደረሱም። ያመጣቸው ታክሲ አንድ የባቡር ጣቢያ ጥሏቸው ተመለሰ።


"ድጋሚ ሌላ ታክሲ ወደ ኬላው እንዲያደርሰን ማነጋገር ያዝን። ነገር ግን ታክሲው ብዙ አልወሰደንም። ትንሽ ከተጓዝን በኋላ ጥሎን ተመለሰ። ያለን አማራጭ በእግር መጓዝ ነበር። ከ30 ኪሎሜትር በላይ በእግራችን ተጉዘናል። ሲነግሩን ሦስት ሰዓት ቢፈጅባችሁ ነው ብለው ነበር። 

ከአምስት ሰዓት በላይ አልተጓዝንም ብለህ ነው?"
ትዕግስት እንደምትለው በመኪና ወደ ፖላንድ የድንበር ኬላ ከመጓዝ በእግር መጓዝ ፈጥኖ ያደርሳል። ምክንያቱም በርካታ ሰዎች መኪናቸውን ይዘው ስለወጡ መንገዱ እጅግ ተጨናንቋል።
"በእግራችን ተጉዘን ድንበር ላይ ስንደርስ ከኛ በፊት በመኪና የወጡ ጓደኞቻችን ገና አልደረሱም ነበር።"

የፖላንድ ኬላ

"በጣም ከምናገረው በላይ ከባዱ የጉዟችን ክፍል የነበረው ድንበር ላይ የገጠመን ነገር ነው። ተስፋ አስቆራጭ ነበር። ከቤታችን ከወጣን ሦስት ቀናት ተቆጥረዋል። ምግብ እንኳን በወጉ አልበላንም። በቂ እንቅልፍ አላገኘንም። ለነገሩ እንቅልፍና ምግብ በዚያ ሰዓት ትዝም አይሉህም።"
ትዕግስት የፖላንድ ድንበር ላይ የነበረው ብርድ 'ለጠላትም የሚመኙት አይደለም' ትላለች።


"ወቅቱ ክረምት ስለሆነ ቅዝቃዜው ከዜሮ በታች [ኔጌቲቭ] ነበር። ጦርነቱ ሳይገለን ብርዱ ይገድለናል ብለን ተስፋ ቆርጠን ነበር። ቀን ቢሆን ብርዱ ትንሽ ይቀንሳል። ይህ ሁላ የሚሆነው በሌሊት ነው።
"እሱን ሁላ ተቋቁመን እንዳናልፍ ደግሞ ድንበር ላይ ያሉ የዩክሬን ወታደሮች ቅድሚያ ለዩክሬናዊያን ነው ብለው ከለከሉን። ያለን አማራጭ ቆመን መጠበቅ ነበር። ከ14 ሰዓታት በላይ ጠብቀናል። ለሴቶችና ሕፃናት ቅድሚያ ይሰጥ ተብሎ እንኳ ለዩክሬናዊያን እንጂ እኛን ዞር ብሎ የሚያየን አልነበረም።"
ትዕግስት ፖላንድና ዩክሬን ድንበር ላይ በታጨቀው ሕዝብ መሃል ፆታዊ ትንኮሳ ይደርስባቸው እንደነበር ትናገራለች።
"ከመጠቅጣችን ብዛት የቆምንበትን መሬት እንኳ አናውቀውም። በዚያ ላይ እኔና ሴት ጓደኞቼ ከፊትና ከኋላ ፆታዊ ትንኮሳዎች ይደርስብን ነበር። እንደ ሴት ከባድ ነበር ሁኔታው። በዚያ ላይ ጥቁር እንደሰው የማይቆጠርበት ቦታ ነበር።"
በስተመጨረሻ ድንበር ለመሻገር የተሰበሰቡ አፍሪካዊያን አመፅ አስነሱ። ቢያንስ ሴቶቹን አሳልፉልን ሲሉ የድንበር ጠባቂዎቹን ተማፀኑ።
"እሺ ቢያንስ ሴቶች ይለፉ ሲባል አጥሩን ዘለን ነው የወጣነው። ከቀናት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ እፎይ ያልነው ፖላንድ ስንገባ ነው።"

ፖላንድ

ትዕግስትና ጓደኛዋ ፖላንድ ከገቡ በኋላ ከዩክሬን የመጡ ሰዎች ወደሚሰባሰቡበት ዋና ከተማዋ ዋርሶው ወደሚገኝ ሴንትራል ስቴሽን የተባለ ባቡር ጣቢያ አመሩ።
"ከዩክሬን እንደመጣን የሚናገር ማህተም ከተደረገልን በኋላ የአንድ የምዕራብ አፍሪካ አገር [ስሙን አልስታውሰውም] ለዜጎቹ ባስ አዘጋጅቶ ነበርና ኢትዮጵያዊያን እባካችሁ ውሰዱን ስንላቸው አሳፍረው ወሰዱን። እዚያ ሁሉም ነገር በነፃ ተመቻችቶ ጠበቀን። የሚበላ የሚጠጣ ነገር አገኘን።"
ትዕግስት ፖላንዳዊያንን አመስግና አትጠግብም።

"ድንበር ከተሻገርን በኋላ ያገኙን ፖሊሾች [ፖላንዳዊያን] ጥቁር ነጭ አይሉም። ሁሉንም ይረዳሉ። ከተማ ከገባን በኋላም ተንከባክበውናል።"
ፖላንድ ከገቡ በኋላ ለሁለት ቀናት ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች ያረፉበት ቦታ አረፉ።


"በሦስተኛው ቀን አንድ አብሮን ከኪዬቭ ጉዞ የጀመረ ካሜሩናዊ አገኘን። 'ፖላንዳዊያን ቤተሰቦች አሉኝ እዚያ አድረን ነገ ወደ ጀርመን እንጓዛለን' ብሎን ወደ ፖላንዳዊያኑ እናትና አባት ሄድን። ኢትዮጵያዊያኑን ተማሪዎች ከዚያ በላይ ማስቸገር አልፈለግንም።
ፖላንዳዊያን በጣም ደግ ነበሩ። እንደ ኢትዮጵያዊ እናት ጉንጭህን፣ ግንባርህን ስማ፤ ምግብ ጠቅልላ የምትሸኝ ፈረንጅ እኔ አይቼ አላውቅም። ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ተነስተው፤ ባቡር ጣቢያ አድርሰውን፤ እንደ አባት፣ እንደ እናት አቅፈውና ስመው ነው የሸኙን።"

ዘረኝነት

ትዕግስት ድንበር ላይ ብቻ ሳይሆን በሰላሙ ጊዜ እንኳ ዩክሬን እያለች የምታስተውለው ዘረኝነት ዓይን ያፈጠጠ እንደነበር ታወሳለች።
"በቋንቋ አትግባባም። የሆነ ነገር ቢገጥምህ የሚደርስልህ የለም። ዩክሬን እያለሁ ደኅንነት ተሰምቶኝ አያውቅም። ለመጀመሪያ ጊዜ በሕይወቴ ከቤት ስወጣ፤ ስራመድ ደኅንነት ሳይሰማኝ የኖርኩበት ቦታ ዩክሬን ነው። እንደውም እኔ ትንሽ ቀላ ስለምል ሕንዳዊ አሊያም ኮለምቢያዊ ነኝ ለእነርሱ። ግራ መጋባት አይባቸዋለሁ። ግን ሌላ ዜጋ ሌላ ዜጋ ነው በቃ።"
ትዕግስት ትቀጥላለች። "ጥቁር ከሆንክ እንደቀልድ ተገድለህ ልትገኝ ትችላለህ። ማንም የሚጠይቃቸው ሰው የለም። መብት የለህም። ሱፐርማርኬት ገብተው 'መንኪ፤ መንኪ' ብለው የሚሳደቡ ሰዎች ናቸው። ያው እንደዛም ሆኖ እንኖራለን ግን ምንም ደኅንነት ተሰምቶን አያውቅም. . . ከባድ አገር ነው።"


ትዕግስት የፖላንድ ድንበር ላይ ከኋላና ከፊት ከሚደርስባቸው ትንኮሳ ባለፈ ዛቻና ማስፈራሪያ ከአእምሮዋ አይጠፋም።
ለምሳሌ ድንበር ላይ የተለያዩ የእርዳታ ድርጅቶች መኪና አዘጋጅተው ይጠባበቁ ነበር። ከዩክሬን ተሰድደው የመጡ ሰዎችን ወደተለያየ ቦታ ለመውሰድ ነበር የሚጠባበቁት። ጀርመን መሄድ ለሚፈልግ የጀርመን መኪና ተዘጋጅቷል። ወደዋና ከተማዋ ለመሄድ ለሚፈልግም እንዲሁ። ነገር ግን ጥቁሮች ሲጠይቋቸው እርዳታ ለመስጠት ፈቃደኞች አይደሉም።

ፍራንክፈርት

ትዕግስት ቤተሰቦቿ አሁንም መቀለ ነው ያሉት። አዲስ አበባም ዘመዶች አሏት። መንገድ ላይ ሳለች የደረሰችበትን ለታናሽ እህቷ ታሳውቅ እንደነበር ትናገራለች።
"ቤተሰብ መጨነቁ አይቀርም። እንኳን እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ላይ ሆነህ ከአዲስ አበባ ወደ አሰላ እንኳን ብትጓዝ ቤተሰብ መጨነቁ አይቀርም። እኔ ያስጨነቀኝ የአባቴ መጨነቅ ነበር። አባቴን በጣም ነው የምወደው። በሕይወት ያለሁ አልመሰለውም ነበር። ለቅሶ ተይዞ ነበር ብልህ ማጋነን አይደለም።"
ትዕግስት አሁን የጀርመኗ ፍራንክፈርት ከተማ አንድ ዘመድ ቤት ተጠልላ ትገኛለች። ከኪይቭ አብራት የወጣችው ጓደኛዋም አብራት ናት።


ጀርመን መግባት ይህን ያህል ከባድ አልነበረም ትላለች። ከፖላንድ ጀርመን የገቡት በባቡር ነው።
ኢትዮጵያ ዩክሬን ውስጥ ኤምባሲ የላትም። እርዳታ ሲያደርግላቸው የነበረው በርሊን የሚገኘው ኤምባሲ ነበር።
"እርግጥ ነው ፖላንድ ከገባን በኋላ ኤምባሲው ተባብሮናል። ዩክሬን እያለን ግን የምንወጣበትን መንገድ እራሳችን ነበርን ማፈላለግ የነበረብን።"
ትዕግስት ወደፊት ምን እንደሚጠብቃት አታውቅም። ለጊዜው የጀርመን መንግሥት ከዩክሬን የመጡ ሰዎችን ተቀብሎ እያስተናገደ ነው።
"ብዙ መንገድ መጥተናል። ብዙ ነገር አይተናል። ከቤት ስንወጣ አንድ ቅይሪ ልብስ ይዘን ነው የወጣነው። አሁንም ቢሆን እግዚአብሔር ያውቃል ብለን በተስፋ ነው የምንጠባበቀው። ኢትዮጵያም ብንመለስ ከዜሮ ነው የምንጀምረው፤ እዚህም ከዜሮ ነው የምንጀምረው። ያው እንደሰው የተሻለ ነገር እጠብቃለሁ።"
ትዕግስት አንድ ነገር እንዳይዘነጋ እፈልጋለሁ ትላለች፡ "የኔን ስለሰማህ እንጂ እህቶቼና ወንድሞቼም ይህንን አሳልፈዋል።"
"እኛ ያየነውን ማንም እንዲያይ አልፈልግም። ለማንም አልመኘውም። መንገድ ላይ ያየናቸው ሕፃናት፤ እናቶች. . . ብዛት በጣም ያሳዝናል። አንዳንዴ በቃላት የማትገልፀውን እንባ ነው የሚገልፀው።
"እኔ እንደውም ብዙ አላማርርም። ትንሽ ጊዜ ነው ዩክሬን የቆየሁት። ሦስት፣ አራት ዓመት ተምረው፤ ሠርተው፤ ገንዘብ ይዘው ይህ ነገር የተፈጠረባቸው አሉ። ሲጀመር እኔ ዩክሬን መቆየት አልሻም ነበር። ቢረጋጋም ተመልሼ አልሄድም። አገር ሰላም ቢሆን ተመልሼ ቤተሰቦቼን መቀላቀል ነው የምፈልገው።"



ምንጭ: ቢቢሲ

አስተያየት ይለጥፉ

0 አስተያየቶች