በደቡብ አፍሪካ ውስጥ በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መሪዎች መካከል ሲካሄድ በነበረው ድርድር ላይ የህወሓት ኃይሎች ትጥቅ እንዲፈቱ ከስምምነት ላይ ተደረሰ።
ለአስር ቀናት ያህል ሲካሄድ በቆየው ድርድር ማብቂያ ላይ በተፈረመው ባለ 12 ነጥብ ስምምነት ላይ በአገሪቱ መኖር ያለበት የጦር ኃይል አንድ መሆን እንዳለበት ከስምምነት ላይ በመደረሱ ነው የህወሓት ኃይሎች ትጥቅ እንዲፈቱ የተስማሙት።
በስምምነቱ መሠረት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ለማረጋገጥ እና የኢፌደሪ ሕገ-መንግሥቱን ለማስከበር ሁለቱ ወገኖች የተስማሙ ሲሆን፤ ይህም “ኢትዮጵያ አንድ ብሔራዊ መከላከያ ኃይል ብቻ አላት” በሚለው ተስማምተናል ብለዋል።
“በመሬት ላይ ያለውን የፀጥታ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት የህወሓት ተዋጊዎችን ትጥቅት ለማስፈታት፣ ተዋጊዎችን ከሠራዊቱ እንዲወጡ ለማድረግ እና መልሶ ወደ ማኅበረሰቡ ለመቀላቀል" ዝርዝር ፕሮግራሞች ላይ ተስማምተና ብለዋል የፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት።
ሁለት ዓመት የዘለቀውን ደም አፋሻሽ ጦርነት ለማብቃት በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መሪዎች መካከል በተደረሰው ስምምነት “የጥይት ድምጽ በዘላቂነት እንዳይሰማ” በመስማማት፣ ጦርነቱ እንዲያበቃ የሚያስችል ዘላቂ የግጭት ማስወገድ ስምምነት ተፈርሟል።
ፖለቲካዊ ልዩነቶችን ለመፍታት በትግራይ ክልል ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲሰፍንና ከዚህ በተጨማሪም በግጭቱ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት ሁለቱ ወገኖች መስማማታቸው ተገልጿል።
ስምምነቱ ይፋ በተደረገበት ሥነ ሥርዓት ላይ የኢትዮጵያ መንግሥትን በመወከል የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ ከህወሓት በኩል ደግሞ የቡድኑ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ፊርማቸውን አኑረዋል።
ቢቢሲ
0 አስተያየቶች