የኢትዮጵያ መንግሥት «ኃላፊነት የጎደላቸው አካላት» ያላቸው ለአደገኛ የፖለቲካ አጀንዳ ሲባል እየፈጠሯቸው የሚገኙ መሠረተ ቢስ ውንጀላዎችን እንደሚያወግዝ አስታወቀ።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ «በምዕራባውያን የተለያዩ አካላት አማካኝነት ኢትዮጵያ ላይ የሚነዛው የሐሰት ስም ማጥፋቶችን» መንግሥት አይታገስምም ብሏል።
መግለጫው አክሎም በእነዚህ አካላት ኢትዮጵያ ውስጥ የከፉ ወንጀሎች ሊፈጸሙ ይችላሉ የሚል «የህወሃትን ጊዜ ያለፈበት ፕሮፓጋንዳ መድገማቸው» አሳፋሪ መሆኑንም አመልክቷል።
«የተሻለ ስም» አላቸው ያላቸው ተቋማትም በኢትዮጵያ ላይ ተቀነባብሮ ይቀርባል ያለውን ይህንኑ የስም ማጥፋት አለማስቆማቸውን አሳዛኝም ብሎታል።
«አስደንጋጭ ክሶችን አቅርቦ የኢትዮጵያ መንግሥትን በማስጨነቅ በህወሃት ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ ለማስቀየስ የሚችሉ መስሏቸው ከሆነ ተሳስተዋል» ነው ያለው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በመግለጫው።
አያይዞም «አንዳንድ ምዕራባውያን ባለሥልጣናትም ጭምር ይህን የሐሰት ክስ የሚነዙት ኢትዮጵያ ትዕዛዛቸውን አልቀበል ስላለቻቸው መሆኑን በይፋ መናገር ጀምረዋል» ብሏል። እንዲያም ሆኖ «ጊዜ አመጣሽ ነው» ያለው «የሐሰት ክስ መሬት ላይ ያለውን እውነት» ጨርሶ እንደማይቀይረውም አጽንኦት ሰጥቷል።
ከቀናት በፊት በዩናይትድ ስቴትስ የጅምላ ፍጅት/ ሆሎኮስት/ ቤተመዘክር ትግራይ ክልል ውስጥ የዘር ማጥፋት ሊፈጸም ይችላል የሚል ማሳሰቢያ አዘል መግለጫ አውጥቷል።
ቤተመዘክሩ ሁኔታው ትግራይ ክልል ውስጥ እየከፋ በመምጣቱ ሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እንዳይባባሱ እና የዘር ማጥፋት ስጋት ሊኖር እንደሚችልም ዘርዝሯል።
ቤተመዘክሩ ያወጣውን ይህን መግለጫ በመቃወም በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ትናንት ይፋዊ ደብዳቤ በማኅበራዊ ገጾቹ አሰራጭቷል። ዛሬ የኮሙኒኬሽን አገልግሎት በመግለጫው የይህን ለመሰለው አደገኛ የስም ማጥፋት ምላሽ ሳይሰጡ ታግሶ ማለፍ እንደማይገባ ነው ያመለከተው።
የኢትዮጵያ መንግሥትም «ያልተረጋገጡ እና ፖለቲካዊ ዓላማ አላቸው» ያላቸውን ውንጀላዎች ከሚያቀርቡ አንዳንድ ሃገራት እና ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት መልሶ ለማጤን መገደዱንም አስታውቋል። መንግሥት በአፍሪቃ ኅብረት ስር ለሚደረገው የሰላም ንግግርም ቁርጠኛነቱን አመልክቷል።
0 አስተያየቶች