ከወራት በፊት (ታህሳስ 25 ቀን 2014 ዓ.ም) ወደ ኢትዮጵያ በመጣበት ወቅት የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረት ከማግኘቱም በተጨማሪ በቦሌ አየር ማረፊያ ልዩ (ቪ አይ ፒ) አቀባበል ተደርጎለት የነበረው ወጣቱ ቀደም ሲል ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ሲፈፅም ነበር።
የ33 ዓመቱ ወጣት ንህላንህላ ላክስ ድላሚኒ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት በመጡ ስደተኞች ላይ ያነጣጠረ እንቅስቃሴ የሚያደርግ ቡድን መሪ ሲሆን በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለበት ምክንያት እስካሁን ግልጽ አልሆነም።
መገናኛ ብዙኃኑ ድላሚኒ የአፍሪካ አንድነት አቀንቃኝ፣ የደቡብ አፍሪካ ማኅበረሰብ መሪ መሆኑን እና በወቅቱ ትኩረትን አግኝቶ የነበረውን #NoMore (በቃ) እንቅስቃሴ ለመደገፍ አዲስ አበባ መግባቱ ተዘግቧል።
ግለሰቡ የሚመራው ቡድን 'ኦፕሬሽን ዱዱላ' የተባለ ሲሆን ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው የውጭ አገር ዜጎች ከደቡብ አፍሪካ እንዲባረሩ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች የሚያደርግ መጤ ጠል ስብስብ ነው።
ግለሰቡ በፖሊስ ተይዞ ጆሃንስበርግ ውስጥ ወደ ሚገኝ የፖሊስ ጣቢያ ሲገባ ለጋዜጠኞች "ሕጋዊ ሂደት እንዲከናወን ፈቃደኛ ነኝ" ብሏል።
ድላሚኒ ጨምሮም የቡድኑ ተከታዮች በእሱ መታሰር ምክንያት ምንም አይነት የኃይል እርምጃ እንዳይወስዱ ጠይቋል።
የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ የቡድኑን ሌሎች መሪዎች ጠቅሶ እንደዘገበው ድላሚኒ ዛሬ አርብ ጠዋት ፍርድ ቤት ይቀርባል ብለው እየጠበቁ ነበር።
ይህ ፀረ ስደተኛ የሆነው ቡድን ችላ ተብለናል ብለው በሚያስቡ የደቡብ አፍሪካ ማኅበረሰቦች ዘንድ ያለው ተቀባይነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑ ይረነገራል።
ነገር ግን ይህ ቡድን የሚያካሂደው በውጭ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ ቅስቀሳ በአገሪቱ ሌላ ዙር መጤ ጠል ጥቃቶችን እንዳይቀሰቅስ ስጋት ፈጥሯል።
ቢቢሲ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በማናገር ባለፉት ቀናት በሰራቸው ዘገባዎች ይህ ቡድን የሚያካሂደው ቅስቀሳ ለደኅንነታቸው አስጊ ሁኔታን እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
0 አስተያየቶች