Ticker

6/recent/ticker-posts

የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ዳግም ተነሳ



የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ  ኃይልና ፋኖ ከትግራይ መከላከያ ሰራዊት ጋር ቆቦ ከተማ  አካባቢ ዛሬ ረቡዕ ነሐሴ 18 ቀን 2014 ዓ.ም በድጋሚ ዉጊያ መግጠም መጀመራቸው ተገለፀ። 


አገልግል ሚዲያ ያነጋገራቸው የቆቦና አላማጣ ከተማ ነዋሪዎች ሰሞኑን በሁለቱም በኩል ተዋጊዎቻቸውን እያስጠጉ መቆየታቸውን ገልፀዋል።


ዶቼቬለ አነጋገርኳቸው  ያላቸው የቆቦ ከተማ ነዋሪዎች ከዚህ ቀደምም የተለመደ ያሉትን የተኩስ ድምጽ መስማታቸውን ተናግረዋል።


ሮይተርስ  አነጋገርኳቸዉ ያላቸዉ ቆቦ አካባቢ የሚኖሩ አንድ ገበሬ በበኩላቸዉ ከዛሬ ጠዋት አንስቶ የከባድ መሣሪያ ድምጽ እየሰማሁ ነው ብለዋል።


ገበሬው፣ ባለፈው ሳምንት የአማራ ልዩ ኃይሎችና ፋኖዎች በአውቶብስ ወደ ግንባሩ ሲሄዱ አይቻለሁ ብለዋልም። ሌላ የአካባቢው ነዋሪም የከባድ መሣሪያ ድምጽ መስማታቸውን ገልጸው ባለፉት ሁለት ቀናት የፋኖ ሚሊሽያና የልዩ ኃይሎች ከፍተኛ እንቅስቃሴ እንደነበር ተናግረዋል። 


የትግራይ ክልል  ቴሌቪዥን ዛሬ ባቀረበው ዘገባ የኢትዮጵያ የፌደራል ኃይል፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሽያዎች ዛሬ ከማለዳው 11 ሰዓት ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ከፍተዋል ሲል ዘግቧል። 


የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ በትዊትር ገጻቸው «የዐቢይ ስርዓት»ያሉት የኢትዮጵያ መንግሥት «በደቡብ ግንባር በሚገኝ ይዞታችን ላይ ጥቃት ሰንዝሯል ብለዋል።


አቶ ጌታቸው በትዊተር ገፃቸዉ በመላው አማራ ክልል የሚገኙ የአማራ ሚሊሽያዎች እና ከወሎ እንደመጡ የጠቀሷቸው ፋኖዎች ከደቡብ እና ስድስተኛው ዕዝ ጋር በመሆን መጠነ ሰፊ ጥቃት ሰንዝረዋል ሲሉ  አስታውቀዋል ። 


ዶቼቬለ የኢትዮጵያ የኮምኒኬሽን ጉዳዮች ባለስልጣናትን ለማነጋገር በተደጋጋሚ ስልክ ቢደውልም መልስ አላገኘም።


ሆኖም ግጭቱ ይካሄዳል የተባለበት የአማራ ክልል የሰሜን ወሎ ዞን ሰላምና ጸጥታ ሃላፊ ኮሎኔል ኃይለ ማርያም አምባው  ግጭት መኖሩን ለዶቼቬለ አረጋግጠዋል።


ግጭቱ የሚካሄደውም በግዳን ወረዳ ጠባብ በር በተባለው አካባቢ መሆኑንም ተናግረዋል። 


ጥቃቱን መጀመሪያ  የሰነዘሩት የህወሓት ተዋጊዎች ናቸዉ ያሉት ኮሎኔል ኃይለ ማርያም የኢትዮጵያ ኃይሎች እየተከላከሉ ነው ብለዋል።


ዶቼቬለ የህወሓት ቃል አቀባይን ለማነጋገር ያደረገው ጥረት በዘገባው ጠቅሷል።

አስተያየት ይለጥፉ

0 አስተያየቶች