የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ዳግም መካሄድ መጀመሩን ተከትሎ TDF በሚል ስያሜ የሚጠሩት የትግራይ መከላከያ ሰራዊት ተዋጊዎች ቆቦ ከተማን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ የወልድያ ከተማ አስተዳደር ከነሐሴ 22፣ 2014 ዓም ጀምሮ የሰዓት እላፊ ገደብ አስቀምጧል።
ሰሞኑን የኢትዮጵያ መንግስት የመከላከያ ሰራዊት፣ ከአማራ ሚሊሻዎችና ከፋኖ ጋር በጥምረት፤ "አሸባሪ" ሲል ከሚጠራው የትግራይ መከላከያ ሰራዊት (TDF) ጋር ጦርነት እያካሄደ መሆኑን ገልፆ ነበር።
ትናንት ቆቦ ከተማን ለቅቆ እንደወጣም መንግስት ገልጿል።
የትግራይ ወታደራዊ ኮማንድ በበኩሉ በፀረ ማጥቃት ዘመቻ ቆቦን፣ ሮቢትንና ዞብልን ጨምሮ ሌሎች ቦታዎችን መቆጣጠሩን ይፋ አድርጓል።
በመሆኑም የወልድያ ከተማ አስተዳደር ይህን ተከትሎ ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የሰዓት እላፊ ገደብ መጣሉን ይፋ አድርጓል።
በገደቡም ከተመደበው የጸጥታ ኃይል በስተቀር ከምሽቱ 1:00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋቱ 12:00 ሰዓት ድረስ ማንኛውም ሰው መንቀሳቀስ እንደማይቻል፤ ለጸጥታ ስራ ስምሪት ከተሰጠው ተሽከርካሪ ውጭ ማንኛውም ተሽከርካሪ ከምሽቱ 12:00 ሰዓት ጀምሮ መንቀሳቀስ የተከለከለ መሆኑን ከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል።
ጦርነቱን ተከትሎ ባለፈው ዓመት በባህር ዳር፣ በወልድያ፣ በደብረ ብርሃንና በሌሎች የአማራ ክልል ከተሞች እንዲሁም በአዲስ አበባ የሰዓት እላፊ ተጥሎ እንደነበር የሚታወስ ነው። በመላ በኢትዮጵያም የአስቸኳይ ጊዜ ታውጆ እንደነበር አይዘነጋም።
0 አስተያየቶች