በሰሜን ኮሪያው ግሎኮም ኮርፖሬሽን የተመረቱ ኹለት የሬድዮ መገናኛዎች ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ወደ ኢትዮጵያ መላካቸው ተነገረ፡፡
በአወሮፓ ሕብረት ማዕቀብ የተጣለበት ድርጅቱ ወደ ኢትዮጵያ የላካቸው የራዲዮ መገናኛዎችን መከላከያ ሠራዊት እየተጠቀመባቸው መሆኑንም ወደፊት ይፋ የሚደረግ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የባለሙያዎች ቡድን ሪፖርት ማረጋገጡ ተነግሯል፡፡
ሥሟ ያልተጠቀሰ የመንግሥታቱ ድርጅት አባል አገር ለባለሙያዎች ቡድን እንዳስታወቀችው፣ ኹለቱ የግሎኮም ራዲዮ መሳሪያዎች ወደ ኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴር በሰኔ 2022 ለአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት አገልግሎት እንዲውሉ ተልከዋል።
የመሳሪያው ዝውውር የተካሄደው አውሮፓ ሕብረት በድርጅቱ ላይ ማዕቀብ በጣለበት ሁኔታ ውስጥ መሆኑ የሰሜን ኮሪያ የስለላ ቢሮ እጅ እንዳለበት ያሳያልም ተብሏል፡፡
የአገር ውስጥ ሚዲያዎች በሕዳር ወር ውስጥ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የግሎኮም ሬድዮ ግንኙነት መሳሪያዎችን ሲጠቀሙ የሚያሳዩ ፎቶዎችን ማዘዋወራቸውም ተሰምቷል፡፡ ከጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ በመሳሪያዎቹ ሲጠቀሙ የሚያሳይ ምስልም ይፋ ተደርጓል፡፡ ይሁንና የአውሮፓ ሕብረት የማዕቀብ መርማሪዎች ከኢትዮጵያ መንግሥት ምላሽ እንዳላገኙ ተነግሯል፡፡
እንደ ኤን ኬ ኒውስ ዘገባ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የመከላከያ ሠራዊት በጉዳዩ ዙሪያ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም። ግሎኮም ኮርፖሬሽንም በተመሳሳይ ለቀረበለት ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አለመስጠቱም ተገልጿል፡፡
ምንም እንኳን ድርጅቱ በማዕቀብ ውስጥ ነው ቢባልም ምርቶቹ ኤርትራን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪካ አገራት በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ እንደሚገኝም ተዘግቧል፡፡
እ.አ.አ ከ2018 ጀምሮ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሰሜን ኮሪያ ላይ አዲስ ውሳኔ አለመወሰኑ ቁጥጥሩን አስቸጋሪ አድርጎታል የተባለ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ጋር በተያያዘው ጉዳይ በቀጣይ ስለሚወሰዱ እርምጃዎ የተባለ ነገር የለም፡፡
0 አስተያየቶች