የትግራይ ኃይሎች ባለፉት ሁለት ቀናት ከጎረቤት ኤርትራ ሠራዊት ጋር አዲስ ውጊያ መካሄዳቸውን አቶ ጌታቸው ረዳ ገለጹ።
የህወሓት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው በትዊተር ገጻቸው ላይ ሰኞ ግንቦት 22/2014 ዓ.ም አመሻሽ ላይ እንዳሉት ባለፈው ቅዳሜ እና እሑድ ማለትም ግንቦት 20 እና 21 ቀን 2014 ዓ. ም. የኤርትራ ሠራዊት በሽራሮ በትግራይ ኃይሎች ላይ ጥቃት ከፍቶ ነበር ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ተካሄደ ስለተባለው ውጊያ መረጃው እንደሌላቸው ለቢቢሲ ገልጸው፣ ነገር ግን የኤርትራ ኃይሎች ጥቃት ሊፈጽሙ የሚችሉበት ሁኔታ የለም በማለት ክሱን ውድቅ አድርገውታል።
ለቢቢሲ እንደተናገሩት የኤርትራ ሠራዊት ጥቃት ሊፈጽሙ እንደማይችሉ አመልክተው “ህወሓቶች ራሳቸው ትንኮሳ ፈጽመው” የሚያሰሙት ክስ ሊሆን ይችላል ብለዋል።
አቶ ጌታቸው በትዊታቸው ላይ ጨምረው ቅዳሜና እሁድ ተከሰተ ካሉት ወታደራዊ ግጭት በተጨማሪ ከአራት ቀናት በፊት ማለትም ግንቦት 16 ቀን 2014 ዓ. ም. የኤርትራ 57ኛ እና 21ኛ ክፍለ ጦር ወደ ትግራይ ክልል ጥቃት ሰንዝሮ እንደነበርና አዲአዋላ በተባለው አካባቢ የትግራይ ኃይሎች ይህንን ጥቃት እንደመከቱ ገልጸዋል።
በጦርነቱ የትግራይ ኃይሎች መልሶ ማጥቃት መፈጸማቸውንና አቶ ጌታቸው በቁጥር የጠቀሷቸው የኤርትራ ወታደሮች መገደላቸውና መቁሰላቸውን እንዲሁም “በርካታ” ያሏቸው የጦር መሣሪያዎችን መማረክ እንደቻሉ አያይዘው ገልጸዋል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽ፣ እንደተባለው በአሁኑ ጊዜ “በኤርትራ በኩል ጦርነት ይከፈታል የሚል እምነት የለንም” በማለት የተከሰተ ነገር ካለም አጣርተው መረጃ እንደሚሰጡ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ለገሰ (ዶ/ር) ጨምረውም የህወሓት ኃይሎች ለጦርነት እየተዘጋጁ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ለዚህ እንዲያመቻቸው ምናልባት በኤርትራ ኃይሎች ላይ ትንኮሳ ፈጽመው ከኤርትራ በኩል ምላሽ ተሰጥቷቸው ሊሆን ይችላል ሲሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
አቶ ጌታቸው በትዊታቸው ላይ የኤርትራ ኃይሎች “ቀጠናውን ወደማያባራ ግጭት እየወሰዱት ነው” ሲሉ የከሰሱ ሲሆን፣ “ይህም ወደ ሰላም ሊደረግ የሚችል ጉዞን የሚያሰናክል” ነው ብለዋል።
ከኤርትራ በኩል ይህንን ክስ በተመለከተ እስካሁን የተሰጠ ምላሽ የሌለ ሲሆን፣ በተጨማሪም ጦርነት ተካሂዷል መባሉን በተመለከተ ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልተቻለም።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ኤርትራ ህወሓት ለዳግም ጦርነት በዝግጅት ላይ እንደሆነ በመግለጽ እራሷን ለመከላከል አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኗን ገልጻ ነበር። ባለፈው መጋቢት ወር የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት አመቺነት ያወጀውን የተኩስ አቁም የህወሓት መሪዎች ከተቀበሉት በኋላ የጎላ ወታደራዊ ግጭት ሳይከሰት ቆይቷል።
ነገር ግን ከሚያዚያ ወር ወዲህ የትግራይ ክልል ከኤርትራ ጋር በሚዋሰንበት አካባቢ ውጥረት እንዳለ ሲነገር የቆየ ሲሆን አልፎ አልፎ የከባድ መሳሪያ ተኩስ ልውውጥ መደረጉ ተዘግቧል።
ሚያዚያ 30/2014 ዓ.ም. የትግራይ ኃይሎች ከኤርትራ ጋር አዋሳኝ በሆኑት አካባቢዎች ላይ የከባድ መሳሪያ ጥቃት ከፍተው ለአጭር ጊዜ የቆየ ወታደራዊ ግጭት መካሄዱን ታማኝ ምንጮች ለቢቢሲ መግለጻቸው ይታወሳል።
በወቅቱ ጥቃቱ ተፈጸመ የተባለው በራማ እና ባድመ አካባቢ ባለው የኤርትራ ጦር ላይ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ ጥቃቱን ተከትሎ በትግራይ ኃይሎችና በኤርትራ ጦር መካከል የተኩስ ልውውጥ መደረጉ ተገልጿል።
ከፌደራልና ከክልል ኃይሎች ጋር ፍጥጫ ውስጥ የሆኑት የህወሓት ኃይሎች፤ መንግሥት ሰብአዊ እርዳታ ያለገደብ ወደ ትግራይ ክልል እንዲገባ ያወጀውን ተኩስ አቁም ተከትሎ ጦርነቶች ጋብ ያሉ ቢመስሉም በድንገት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት አለ።
ምንጭ:- ቢቢሲ
0 አስተያየቶች