Ticker

6/recent/ticker-posts

የዩክሬን የኒውክሌር ጣቢያ ከቁጥጥር ውጭ መውጣቱን ተመድ አስታወቀ


 

ሩሲያ ዩክሬንን በወረረችበት ወቅት የተቆጣጠረችው ግዙፍ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ሙሉ በሙሉ ከቁጥጥር ውጭ መውጣቱን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኒውክሌር ኤጀንሲ ኃላፊ ተናገሩ።

 

ዛፖሪዝሃያ የኒውክሌር ጣቢያ ምርመራ እና ጥገና እንደሚያስፈልገው ኃላፊው ራፋኤል ግሮሲ መናገራቸውን አሶሼትድ ፕሬስን ጠቅሶ ቢቢሲ ዘግቧል።

 

“በየትኛውም የኒውክሌር ጣቢያ ውስጥ ፈጽሞ መከሰት የሌለባቸው በርካታ ነገሮች እየተፈጸሙ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

 

የአውሮፖ ትልቁ የኒውክሌር ጣቢያ ለውጊያዎች ቅርብ መሆኑም ከፍተኛ አደጋ ደቅኗል።

 

የአሜሪካ  የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በዚህ ሳምንት ሩሲያ በመጋቢት ወር የተቆጣጠረችውን የኒውክሌር ጣቢያ እንደ ጦር ማዕከልነት በመጠቀም የዩክሬን ኃይሎች ላይ ጥቃት እየፈጸመች ነው ሲሉ ከሰዋል።

 

የዩክሬን ባለሥልጣናት በበኩላቸው ሩሲያውያን በኃይል ጣቢያው ውስጥ ጦሩን በማስፈር እንዲሁም የጦር መሣሪያዎችን ማከመቻ አድርገውታል ብለዋል።

 

ነገር ግን ግዛቲቱን እንዲያስተዳድሩ በሩሲያ የተሾሙት ባለሥልጣን ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት የዩክሬን ኃይሎች ከምዕራቡ ዓለም በድጋፍ ያገኙትን የጦር መሣሪያዎች ተጠቅመው ጣቢያውን ለማጥቃት እየሞከሩ ነው ሲሉ አስተባብለዋል።

 

አስተዳዳሪው የገኒ ባሊትስኪ እንዳሉት ለዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ኃላፊ ለራፋኤል ግሮሲ ሩሲያውያን የኒውክሌር ተቋሙን እንዴት እየጠበቁ እንደሆነ እንዲሁም የዩክሬንን ጥቃት ለማሳየት ዝግጁ መሆናቸውን አስረድተዋል።

 

ሩሲያ ጣቢያውን በተቆጣጠረችበት ወቅት የማዕከሉን ሕንፃ በጦር መሣሪያ መደብደቧን ተከትሎ ዓለም አቀፍ ወቀሳ ማስከተሉ ይታወሳል።

 

የኒውክሌር ጣቢያው አሁንም በሥራ ላይ ሲሆን ያሉትም የዩክሬን ሠራተኞች በሩሲያ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ይገኛሉ።

 

ራፋኤል ግሮሲ በኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጽሕፈት ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ “ሁኔታው በጣም ተለዋዋጭ ነው፣ እያንዳንዱ የኒውክሌር ደኅንነት መርሆች በአንድ መንገድ ወይም በሌላ መንገድ ተጥሰዋል እናም ይህ እንዲቀጥል መፍቀድ አንችልም” ብለዋል ።

 

ኃላፊው ጣቢያውን ለመጎብኘት የልዑካን ቡድን ለማዋቀር እየሞከሩ ቢሆንም ነገር ግን የዩክሬን እና የሩሲያ ኃይሎችን ፍቃድ ከማግኘት በተጨማሪ የጦር ቀጠናውን ለመጎብኘት ካለው አደጋ አንጻር የተባባሩት መንግሥታት ይሁንታንም ይጠይቃል።

 


አስተያየት ይለጥፉ

0 አስተያየቶች