ሱዳን በኢትዮጵያ አየርመንገድ በኩል የገቡትን የጦር መሳሪያዎች ሕጋዊነት አረጋገጠች
የሱዳን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ ካርቱም የገቡት የጦር መሳሪያዎችን የያዙ ከ70 በላይ ሳጥኖች ሕጋዊ ናቸው ሲል አረጋገጠ።
ቅዳሜ በካርቱም አየር ማረፊያ የጉምሩክ ባለሥልጣናት በሕገ ወጥነት መያዛቸው የተዘገበው የጦር መሳሪያዎች ሕጋዊ ፈቃድ ባለው የጦር መሳሪያ ነጋዴ የመጡ መሆናቸውን የሱዳን መንግሥት መግለጹን ሮይተርስ ዘግቧል።
የሱዳን ዜና አገልግሎት ሱና በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጓጉዘው ሱዳን የገቡት የጦር መሳሪያዎች "በሱዳን መንግሥት ላይ ወንጀል ለመፈጸም" ጥቅም ላይ ሊውሉ ነበር የሚል ጥርጣሬ አለ ሲል ዘግቦ ነበር።
መነሻውን ከአዲስ አበባ አድርጎ ቅዳሜ ምሽት ካርቱም ባረፈው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ውስጥ ተጭነው የነበሩት የጦር መሳሪያዎች በሱዳን ጉምሩክ ባለሥልጣናት እንደተያዙ ሱና በዘገባው አመልክቷል።
ሱዳን በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል ካርቱም ከገቡ በኋላ ተይዘዋል ስላለቻቸው የጦር መሳሪዎች ምርመራ እያደረኩ ነው ስትል አስታውቃ ነበር።
የኢትዮጵያ አየር መንገድም ወደ ሱዳን ካርቱም ያጓጓዛቸው የጦር መሳሪያዎች ሕጋዊ ናቸው ሲል ሰኞ ረፋድ ላይ ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥቶ ነበር።
አየር መንገዱ እንዳለው መሳሪያዎቹ ወታደራዊ ሳይሆኑ ለአደን አገልግሎት የሚውሉ ከመሆናቸው በተጨማሪ አስፈላጊው ሕጋዊ የመጓጓዣ ሰነድ ያላቸው ናቸውም ብሏል።
ሰኞ አመሻሽ ላይ የሱዳን የአገር ውስጥ ሚኒስቴርም መሳሪያዎቹ 'ዋኤል ሻምስ ኤልዲን' በተባለ ፈቃድ ባለው የመሳሪያ ነጋዴ ድርጅት አማካይነት በሕጋዊ መንገድ የገቡ መሆናቸውን አረጋግጧል።
ምንም አስተያየቶች የሉም