ሱዳን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያስገባውን የጦር መሳርያ በቁጥጥር ስር አዋልኩኝ አለች፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበኩሉ መሳሪያው ህጋዊ ነው ብሏል፡፡
በኢትዮጵያ አየር መንገድ የጭነት አውሮፕላን ተጓጉዞ ሱዳን የገባ እና «በመንግስት ላይ ወንጀል ለመፈጸም» ያሴረ ነበር ያሉትን የጦር መሳርያ በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን የሱዳን ባለስልጣናት ትናንት እሁድ አስታወቁ።
ሮይተርስ የሱዳን የዜና አገልግሎት ሱናን ጠቅሶ እንደዘገበው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጭነት አውሮፕላን 72 ሳጥኖች የጦር መሳርያዎችን ከኢትዮጵያ ወደ ሱዳን አጓጉዟል።
የምሽት አጉሊ መነጽሮችን ጨምሮ በጠመንጃዎች የተሞሉት ሳጥኖች ከትናንት ወዲያ ቅዳሜ ምሽት ካርቱም መድረሳቸውን ዘገባው አመልክቷል። በአየር መንገዱ ተጓጓዟል የተባለውን የጦር መሳርያዎች ጭነት የሚመረምር ኮሚቴ መዋቀሩን ሱናን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል።
የጦር መሳርያው ከሞስኮ ተጓጉዞ ኢትዮጵያ የደረሰው በጎርጎርሳውያኑ ሚያዝያ 2019 በሱዳን ህዝባዊ አመጽ ከተቀሰቀሰ በኋላ እንደነበር ደርሼበታለሁ ሲል በጦር መሳርያው ላይ ምርመራ በማድረግ ላይ የሚገኘው ኮሚቴ አስታውቋል።
የጦር መሳርያዎቹ «በዲሞክራሲያዊ የሽግግር ወቅት ላይ የሚገኘውን የሀገሪቱን መንግስት ለማደናቀፍ ያለመ ነው።» ሲል በምርመራ ላይ የሚገኘው የሱዳን ኮሚቴ ገልጿል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበኩሉ የጦር መሳርያዎቹ ለአደን አገልግሎት የሚውሉ እና ሕጋዊ የማጓጓዣ ሰነድ ያላቸው ናቸው ሲል የቀረበበትን ውንጀላ አስተባብሏል።
አየር መንገዱ ባወጣው መግለጫ እንዳለው የጦር መሳርያዎቹን ህጋዊነት ለማጣራት ለረዥም ጊዜ በአዲስ አበባ እንዲቆይ ማስገደዱን ጠቅሶ ለጊዜው በስም ያልተጠቀሰ የመሳርያ አጓጓዥ ወኪል አየር መንገዱን በአንድ የሱዳን ፍርድ ቤት መክሰሱን አመልክቷል።
የጦር መሳርያዎቹን በጊዜ አላጓጓዘልኝም ሲል የ250,000
ዶላር የካሳ ክፍያ አየር መንገዱን እንደጠየቀም ገልጿል።
የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ ዲና ሙፍቲ ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ሰዓት ድረስ በጉዳዩ ላይ አስተያየት አልሰጡበትም።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመንግስት ወታደሮችንና የጦር መሳሪያዎችን ወደ ትግራይ
አጓጉዛል በሚል በቅርቡ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ትችት ሲቀርብበት እንደነበር ይታወሳል፡፡
ምንም አስተያየቶች የሉም