Ticker

6/recent/ticker-posts

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነቱ እያስከተለያለው ሰብዓዊ ቀውስ እየተባባሰ ነው - የዓለም ጤና ድርጅት

በሰሜን ኢትዮጵያ የተነሳው ጦርነት ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ መምጣቱንና እስከ ሰባት ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ተናግረዋል። 


በመላው ትግራይ፣ አማራ እና አፋር እስከ ሰባት ሚሊዮን የሚደርስ ህዝብ አስቸኳይ የምግብ እና የሌሎች እርዳታ ፈላጊዎች መሆናቸውንም ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሐኖም አስረድተዋል። 


አንድ ዓመቱን ሊደፍን ሳምንታት በቀሩት ጦርነት ስድስት ሚሊዮን የሚሆን የትግራይ ህዝብ ለችግር እንደተጋለጠና በክልሉም አንድ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ የመሰረታዊ ፍላጎት ክልከላ በመጣሉ መብራት፣ መንገድ፣ ባንክ እና ቴሌኮምን ጨምሮ መሰረታዊ አገልግሎቶች ተቋርጠዋል ብለዋል።

ለህክምና መቐለ ወደሚገኘው ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል የገቡ ታማሚዎችም በመድኃኒት እጦት ሳቢያ ህይወታቸው አልፏል ብለዋል። 


ወደ ክልሉ የሚወስዱ መንገዶች በመዘጋታቸውም የእርዳታ እህልና መድኃኒት በሚያስፈልገው ያህል ወደ ክልሉ እየገባ አይደለም ብለዋል። 


መንግሥትና ከመንግሥት ውጭ ያሉ አካላት በሚያደርጉት ክልከላ ወደ ክልሉ እየገባ ያለው የእርዳታ እህል 10 በመቶ ብቻ ነው ሲሉም ዶክተር ቴድሮስ ገልፀዋል። 


በትግራይ እና በፌደራል መንግሥት መካከል የተነሳው አውዳሚ ጦርነት ከሶስት ሳምንታት በኋላ አንድ ዓመት ይሞላዋል። 


ኤርትራን ጨምሮ ሶስት ሃገራት በቀጥታና በተዘዋዋሪ በጦርነቱ መሳተፋቸውን መረጃዎች ያሳያሉ። 


በአሁኑ ወቅት አውዳሚው ጦርነት ወደ ዓፋርና አማራ ክልሎች ተስፋፍቶ በሚልዮኖች የሚገመቱትን ለርሃብና ስደት ዳርጓል።


አስተያየት ይለጥፉ

0 አስተያየቶች