Ticker

6/recent/ticker-posts

በኢትዮጵያ የጉዞ ጥንቃቄ እንዲደረግ ዩናይትድ ኪንግደም አስጠነቀቀ

የዩናይትድ ኪንግደም(ዩኬ) መንግሥት በኢትዮጵያ ውስጥ በመላው ትግራይ ክልል እንዲሁም በ30 ኪሎ ሜትር ድንበር ላይ በሚገኙ አማራና በአፋር ክልሎች ላይ የሚገኙ አካባቢዎች መንገደኞች እንዳይጓዙ መከረ። 


ፎሬይን፣ ኮመንዌልዝ ኤንድ ደቨሎፕመንት ቢሮ (ኤፍሲዲኦ) ሰኞ ጥቅምት 01/2014 ዓ.ም ባወጣው የጉዞ ማሳሰቢያ በሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ጦርነት ምክንያት በትግራይ፣ አማራና አፋር ክልሎች ውጊያዎች እየተካሄዱ ነው ብሏል። 


ውጊያው በፍጥነት የመዛመት አዝማሚያ እንዳለውም ጠቅሶ ከዚህም ጋር በተያያዘ በአጠቃላይ ወደ ትግራይ እና 30 ኪሎሜትር ርቀት ባሉ የአማራና የአፋር ድንበር ግዛቶች አንዳይጓዙ መክሯል። 


እንዲሁም በአማራ በአፋር ውስጥ ውጊያዎች እየተካሄዱባቸውና ሊካሄዱባቸው በሚችሉ ስፍራዎች ዜጎችና ሠራተኞች እንዳይጓዙ ምክር አስፍሯል። 


በአማራ ክልል የተጠቀሱት ስፈራዎች ሰሜን ወሎ ዞን፣ ዋግ ኽምራ ዞን፣ አምባሰል፣ ተሁለደሬ እና ደሴ ወረዳዎች፣ እብናት፣ ከምከም፣ ላይ ጋይንት፣ ፋርጣ፣ ፎገራ፣ ደቡብ ጎንደር ዞን ጋይንት ወረዳዎች፣ ዓዲ አርቃይ፣ በየዳ፣ ደባርቅ፣ ደባት፣ ወገራ፣ በላሰ፣ ጃናሞራ፣ ሳንጃ ወረዳዎች እና ሰሜን ጎንደር ዞንን ያካትታል። 


ከዚህም በተጨማሪ በአፋር ክልል መላው ዞን 4፣ በዞን አንድ የጭፍራ ወረዳና ዳሎል፣ ኩኔባ፣ አባአላና በዚን 2 ሜጋሌ ይገኙበታል። 


ሆኖም ኤፍሲዲኦ በቀሪዎቹ አማራና አፋር ክልሎችም ቢሆን ጦርነቱ ያለ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሊዛመት ስለሚችል አስፈላጊ ካልሆነ እንዳይጓዙ ማስጠንቀቂያውን አስቀምጧል። 


ለዜጎቹም በወታደራዊ እንቅስቃሴ አካባቢ ውስጥ ከሆኑ እና በደህና መውጣት ካልቻሉ፣ በቤት ውስጥ ለደኅንነታቸው አስተማማኝ በሆኑ ስፈራዎች ላይ እንዲቆዩና አካባቢዎቹን ለመልቀቅ የሚያስችሉዎ ሁኔታዎች በንቃት መከታተል እንደሚገባቸውም አስታውቋል። 


ከዚህም በተጨማሪ የትግራይ ተወላጆች በአውሮፕላን ማረፊያም ሆነ ፖሊስን ጨምሮ በባለስልጣናት ከፍተኛ ምርመራም ሆነ እስርም ሊያጋጥማቸው ስለሚችል የባለስልጣናቱን መመሪያ እንዲከተሉ አሳስቧል። 


ጦርነቱ እየተካሄደበት ካለበት ከሰሜን ኢትዮጵያ በተጨማሪ መረጋጋት አይታይባቸውም በተባለባቸው በጋምቤላ ክልል አራት ወረዳዎች፣ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን፣ ነቀምቴ ከተማ ምሥራቅ ወለጋ መንገደኞች እንዳይጓዙ መክሯል። 


በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል፣ ሶማሌ ክልል የተወሰኑ ቦታዎች፣ በደቡብ ሱዳን ድንበር አካባቢ፣ ኢትዮጵያ ሶማሊያና ኬንያ በሚዋሰኑበት ድንበሮችም መንገደኞች እንዳይሄዱ ከተጠቀሱት ስፈራዎች ይገኙበታል። 


በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በኮንሶ ዞን እና በአካባቢው የተካሄዱ የትጥቅ ግጭቶችን ተከትሎ ውጥረት መንገሱንና በመተከል ዞን የተከሰተውን የትጥቅ ጥቃትን ተከትሎ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውጥረቱ መፈጠሩንም ጠቅሶ ከሁኔታው እንዲጠነቀቁ አሳስቧል። 


ከዚህም በተጨማሪ አሸባሪዎች በኢትዮጵያ ላይ ጥቃ ሊፈፅሙ እንደሚችሉም ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። 


አሸባሪዎች በኢትዮጵያ ጥቃት ለመፈጸም ሊሞክሩ እንደሚችሉ የጠቀሰው መግለጫው ጥቃቶቹ በዘፈቀደ ሊሆኑ እንደሚችሉና የውጭ ዜጎች በብዛት ሊያዘወትሯቸው በሚችሉ ቦታዎች ሊፈጸሙ ይችላሉ ብሏል። 


ከዚህም ጋር በተያያዘ በተጨናነቁ አካባቢዎች እና በሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች እንደ የትራንስፖርት ማዕከሎች ፣ ሆቴሎች፣ ምግብ ቤቶች፣ ቡና ቤቶች እና የአምልኮ ቦታዎች እና እንደ ሐይማኖታዊ ወይም የስፖርት ዝግጅቶች ባሉ ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ሁልጊዜ ንቁ ሆኖ መጠበቅ እንደሚገባ አስጠንቅቋል። 


ከዚህም በተጨማሪ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል እና በደቡባዊ ድንበር ከኬንያ በምትዋሰንበት ቦታ የአፈና ስጋት ስላለ ወደዚያም አካባቢ እንዳይሄዱ ምክር ተሰጥቷል።


ምንጭ:- ቢቢሲ

አስተያየት ይለጥፉ

0 አስተያየቶች