ትዊተር በኢትዮጵያ ካለው የሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ የተወሰኑ አካውንቶችን ማገዱን ለቢቢሲ አረጋግጧል።
ትዊተር የታገዱትን አካውንቶች ትክክለኛ አሃዝ ባይሰጥም የትግራይ ደጋፊ ተጠቃሚዎች ግን የታገዱት አካውንቶች በመቶዎች ሊቆጠሩ እንደሚችሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
የማኅበራዊ ሚዲያ ኩባንያው ይህንን እርምጃ የወሰደው "የትዊተርን ሕግ በመጣስ፣ የተወሰኑ ሃሽታጎች እና የትዊተር ገፆችን በትዊቶች ውስጥ በተደጋጋሚ በአላስፈላጊ ሁኔታዎች በማካተታቸው ነው" ሲል ለቢቢሲ አስረድቷል።
"በኢትዮጵያ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተገናኘ በትዊተር ላይ የሚደረጉ ውይይቶች ደኅንነታቸው በተጠበቀ መልኩ እንዲሄድ ከምናደርገው ጥረት ጋር የተገናኘ ነው" ብሏል።
በትዊተር ተሰሚነት ያላቸውና ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በሚደረገው ጦርነት የትግራይ ኃይሎችን የሚደግፉ አንዳንዶችም በመቶዎች የሚቆጠሩ ተከታዮችን በማጣታቸው ቅሬታ ያሰሙ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ጓደኞቻቸው ከትዊተር መታገዳቸውን በተመለከተ ወቀሳ አቅርበዋል።
አብዛኞቹ የታገዱት አካውንቶች የትግራይ ደጋፊዎች የሆኑ ቢመስሉም፣ ትዊተር የሕጎቹን አተገባበር በተመለከተ "በተጨባጭ በአካውንቶቹና ይዘቶቹ ላይ ያተኮሩ" መሆናቸውን ገልጾ "ከፖለተካዊ ማንነት እና ርዕዮተ ዓለም ገለልተኞች ነን" ብሏል። የታገዱ አካውንቶችን በተመለከተ ይግባኝ ማለት እንደሚቻል ተጠቅሷል።
ከቅርብ ወራት ወዲህ የማኅበራዊ ሚዲያዎች ጥላቻን እና ቅስቀሳዎችን ለማስፋፋት መድረኮቻቸው መጠቀሚያ መሆናቸው ላይ እርምጃ መውሰድ አልቻሉም በሚል ትችት እየደረሰባቸው ይገኛሉ።
በኅዳር ወር ላይ ትዊተር በከፍተኛ ሁኔታ ታዋቂነት ያገኘ ርዕስ 'ትሬንድ' የሚያደርግበትን አሰራር በኢትዮጵያ ለተወሰነ ጊዜ አቋርጦ ነበር።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በስድስት ወራት ውስጥ ኢትዮጵያን በሚመለከቱ ከ92 ሺህ በላይ የፌስቡክ እና ኢንስታግራም ይዘቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን ፌስቡክ በኅዳር ወር መግለጹ ይታወሳል።
እርምጃው የተወሰደው የድርጅቱን የጥላቻ ንግግርን ደንብን በጣሱት ላይ መሆኑን እና 98 በመቶ ያህሉ በሌሎች ሪፖርት ከመደረጉ በፊት እንደተደረሰባቸው ጠቅሷል።
ዓለም አቀፉ ማኅህበረሰብ በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ መከታተል የጀመረው አሁን ሊሆን ቢችልም ፌስቡክ ግን "ከሁለት ዓመታት በላይ በአገሪቱ ውስጥ ከነበሩት አስከፊ የግጭት ስጋቶች አንጻር የሰዎችን ደኅንነት ለመጠበቅ የሚያስችል አጠቃላይ ስትራቴጂን በመተግበር ላይ ቆይተናል" ብሏል።
በዚህም ከሁለት ዓመት በፊት ኢትዮጵያን "ለግጭት እና ለአመጽ ከፍተኛ ተጋላጭ ናቸው ብለን ወደምናምንባቸው አገራት ምድብ አሸጋገረናታል" ብሏል።
ደርጅቱ የተቋሙን ፖሊሲዎች የሚጥሱ ይዘቶችን በማስወገድ፣ የሰዎችን ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን በመደገፍ እና ሰዎች ኦንላይንም ሆኑ አልሆኑ ደኅንነታቸው እንዲጠበቅ ትኩረት አድርጎ መስራቱን አክሏል።
ምንጭ:- ቢቢሲ
0 አስተያየቶች