Latest

ads header

ዜና

"እዉነት ከመንበርህ የለህማ" ገጣሚ ሙሉጌታ ተስፋዬ

                                                                  

                              "እዉነት ከመንበርህ የለህማ"

                                 ገጣሚ ሙሉጌታ ተስፋዬ 

ገጣሚ ሙሉጌታ ተስፋዬ


ምነዋ መንግሰተ ሰማይ! የምህረትሽ ቀን ራቀ?

ምነው ትንግርትሽ ረቀቀ ?

ምነው ኪዳንሽ ታጠፈ … ወዝሽ ወዘናሽ ነጠፈ?

እንደ ዳጉሳ ድፍድፍ … ላቦትሽ ተንጠፈጠፈ

አሳርሽ ጠሎ አሰፈፈ

ምነው እርሾው ተሟጠጠ …. ጎታው ጎተራው ታጠጠ

ረሀብ ላንቃው ፈጠጠ … ያዳም ልጅ አፅሙ ገጠጠ

ምነው ጭር አለ ቀየው! ሀሩር ነዲዱ በረታ

ኮርማው ጥማዱ ተረታ

ምነው ነበልባሉ አየለ … ማሳው ተንቀለቀለ

ነቀለ ሞፈር ሰቀለ! ተግድራ ደቀለ

ምነው ምድር ጨነገፈች … ዝላ ተርገፈገፈች?

ካስማ እንደተደገፈች ምነው ሳታብብ ረገፈች፡፡

ምነው የናት ጡት ደረቀ … አራስ ልጅ ተስረቀረቀ

ምነው አንጀቱ ታለበ … በውኑ ተለበለበ

ኮሶ ስንብቱን ለለበ

ምነው ወላድ ተንሰለሰለ … ልሳነ ቃሉ ሰለለ

በቁሙ ከስሞ ከሰለ፡፡

አቤት የርግማን ቁርሾ …

በንጣይ እርሾ መነሾ

ምነው ላይፀድቅ በቀለ?

የሰው ልጅ ዋጋ ቀለለ

ትቢያ አፈር ተቀላቀለ፡፡

ሆድና ጀርባው ተጣብቆ

አንጀቱ በራብ ተሰብቆ

እንደፈረሰ ክራር ቅኝት

ሰርቅ እንዳነቀው ድብኝት

ወለሰ! ስልቱ ስለቱ

ሰው፡

ያ ሰው ጠንካራው ብረቱ

የጥንት የጥዋት የመሰረቱ፡፡

ውሳኔው ተርመጥምጦ፣

ተፈጥርቆ ተዳምጦ

ተሞዥርጎ ተሸምጥጦ

ምነው ጓሽቶ ሆመጠጠ

እንደ በሬ ጨው ሆረጠ?

ባፍላው ተዝለፍልፎ አረጠ፡፡

እንደ መወክል አጎዛ … በችንካር ተገድግዶ

ይግባኝ እንዳይል ታግዶ

እንደወይራ ፍልጥ ተማግዶ

ምነው ኩክ ብሎ ሳይነቃ … ምነው ሳይጠረቃ መከከ

በስሎ ሳይሰላ ደከከ፡፡

ተፈጥሮ ፊቱን ጨፍግጎ

እንደ ግራዋ ስር መርግጎ

ሁዳዱን እያነደደ

አቤት ባዩን እያሳደደ

እንደ ግራ ግመሬ … በነፍር ጥፍሩ እየለቀመ

የረጨነውን እየቃመ

ጉልማችንን ሲያመክነው

ወረታችንን ሲያበክነው

እኮ ማንን ልንኮንን ነው?

የመቅሰፍት ደመና ሰሮ … ሽቅብ ጠቅሶ ሲያርመሰምስ

እንደ ወረግ ተደርምሶ እያንቃቃ እኛን ሲያምስ

ወገብ ከፍሎ … ደረት ገምሶ

አቅም ሲከላን አቅምሶ

እኮ! እስከመቼ እግዚእትነ

እኮ! እስከመቼ ኪራራይሶ?

የቀን ጨለማ ሲወረን

እህል ሸማኔው ደውሮ … ለጆቢራ ሲወረውረን

አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶ … ቀሪ ወሬ ነጋሪ የሚያሳጣን

እኮ! ምን በድለን? ምን አጥፍተን? ምን በወጣን?

የምን ቅጣት ነው ይሄ? ቀጥፎ እንደተያዘ ጩልፋት

አርሰው አደፍርሰው በበሉ … የምን የራብ ትሩፋት

ከንቱ ውዕቱ ልፋት፡፡

እኮ እንደ ኖህ ዘመን ንፍር ውሃ

ዘር ሳይተኩ ታክቶ መጥፋት?

ምነው ዲበኩሉ ቤዛ ዓለም

ጎህ ቀዶ በቀን መጨለም?

በጠኔ ርዶ መስለምለም?

እኮ ያንጀትን ባንጀት መፋለም?

ምነው? ምነው አዛውንቱ በየጉድባው

ጋሜው ድምድሙ ኮበሌው … በየጥጉ በየደረባው

ወድቆ ደርቆ ሲነፈራ

ምነው ተፈጥሮስ ጡር አትፈራ?

ምን ይሉታል ይሄን ብይን? … አንቀጽ ገልፆ ሳያጣቅስ

ምን ይሉታል ይሄንን ፍርድ …

እንዲህ ያለ ጉድ አለ'ንዴ?

እግዜር ወንዱ … እግዜር መንዴ!

ደረቅ ጡት እየጠባን ቁረንጮ ስንገተግት

ከመንግስተ ሰማይ የምህረት ግት፡፡

ምነው የማርያም ልጅ … የስርየትህ ቀን ራቀ

ምነው ታምርህ ረቀቀ?

በየጥሻው ተወትፈን … እንደተምች ስንረፈረፍ

ቅኔ በበቀቀን ሲዘረፍ

አቀርቅረን ስናንቋርር

ቅሪታችንን ስናንቃርር

እንደ ቀላጤ አከንባሎ …

ቁልቁል ባፍጢም ተተክለን

በእርኩስ አመዳይ ተበክለን

እንዲህ የትም ስንቀር እያየህ ዝም ካልክማ

እውነት … እውነት ከመንበርህ የለህማ!

እንደ ሰባራ ቅል ደቀን

ድበን በራብ ተደቅድቀን

እርሻው ማረሻው ሲከዳ … ሰማይ መሬቱ ሲያብል

እያየህ ዝም ካልከኝ …. እኔስ እንደሌላው የለህም ብል

ምንተዳየ ብትፈርድብኝ

መቸም አሽተህ አትቅመኝ

እንደውልብኝ

ናዳ እንደሚጥል ጫላዳ … ድርቅ ሲሳለቅብን

እየነዳ እያነደደ … የገሞራ ድኝ ሲለቅብን

እያየህ ዝም ካልክማ …

እውነት … እውነት ከመንበርህ የለህማ!

ጀንበር ትንታጓን ረጭታ … ሰብ ዓለሙን ስትፈጀው

አብ ወልድህ ቃልህ ካልባጀን

ድርሳን ትንቢትህ ካልዋጀን

አንተስ ምንህ መለኮት … እኔስ ለምን ያንተ ባሪያ

ሆዴን ሁዳዴን ላምልክ እንጂ …

ትንሳኤ እንደሌለው እሪያ

ያንተን ጉድማ አየሁት

ያንተን ጉድልማ ለየሁት

ማረኝ ሲሉት የሚመር … የማይታደግ አላመልክም

ወትሮም የተማረ ቄስ እንጅ … የሰው ልጅ መላክ አይልክም

ለካ ሲያጋልጥ ይቆምጣል … ወራት ሲጥል ይከፋል

እንዳመለ ጉድጓድ እህል … ሞት በክቶ ይከረፋል፡፡

ለካስ ሰውነት ባዳ ነው

ለካስ ሰው መሆን እዳ ነው

እህል ውሃ ቢያደነድነው

ሲያጣ ሲነጣ በድን ነው፡፡

የኛስ ይሁን እንዳሻው፡-

ለእጥፍ ፈተና ከፈጠርከን፤

ለፍታችሁ ተፍታችሁ ኑ ካልከን

ለቀብር አፈር ከወጠንከን፡፡

ግን ፡- ግን … ብላቴናዎች ምን በደሉ?

የማንን አደራ በልተው … የማንን አማና አጎደሉ?

እምብርታቸው ያላረረ … አጥንታቸው ያልከረረ

ሰማይ በቀል እንደቋጠረ … እጣቸውን እየመነጠረ

መንገዳቸውን በእሾህ እያጠረ

እንደ ደራሽ ውሃ አግተልትሎ

በራብ አኮርባጅ ተልትሎ

ከእናት እቅፍ በግፍ ነጥቆ

ምሱን ሲቃመስ ተባጥቆ

ሲሰለፍብን ባጭር ታጥቆ

እያየህ ዝም ካልክማ …?

እውነት … እውነት ከመንበርህ የለህማ!

እንደ ታዛ ሥር ሰንሰል አሰልስሎ እያበሰበሰ

እንደ ሙሬ እየጠረገ … እያጋበሰ

የዘፀዓት ትንቢቱ ደርሶ ሰብ ዓለም ከል ከለበሰ

በማን ሊዳኝ ነው ቅጣቱ

የሰው ዘር አንዲት ቅንጣቱ

ያባወራ ባለ አውራ ጣቱ፡፡

እንደ በልግ አውድማ ነዶ … ምድር ለቅልቆ ከምሮ

ነፍስ ከእስትንፋስ ነጥሎ … ሲኦል እቶን ውስጥ ሞጅሮ

በነበልባል መንሽ እየዘራ በረሀብ አራገበው

ሰው እርጥቡን አንገበገበው፡፡

ነፍስ ይማር እርካቡ ረገበ

ቀብርም አስከሬን ጠገበ

ፀሀፊም ድርሳን ዘገበ፡፡

ጥንብ አንሳን ግብር ጠርቶ በራሪ ጋር ይወዳጅበት

ስለት እንደዋጀበት እያጋፈረ ይባጅበት

ወትሮም የሞት ምሬትን ያልቀመሰ …

የራብ እሳት አይዋጅብበት

እንዲህ አይንን ጡር እያስከፈለ

እንደ በቆሎ እሸት እየጠበሰ እየፈለፈለ

ባይበላውም ያባለው!

መቸም ተጠቀም አላለው

አይ ወልዴ አባ ግድ የለው፡፡

በየጥሻው ተወትፈን፣ እንደተምች ስንረፈረፍ

ቅኔ በበቀቀን ሲዘረፍ

አቀርቅረን ስናንቋርር፣

ቅሪታችንን ስናንቃርር

እንደቀላጤ አከንባሎ ቁልቁል ባፍጢም ተተክለን

በእርኩስ አመዳይ ተበክልን

እንዲህ የትም ስንቀር እያየህ ዝም ካልክማ

እውነት … እውነት ከመንበርህ የለህማ!

1987 ዓም

* * *

 

ገጣሚ ሙሉጌታ ተስፋዬ

(“የባለቅኔው ምህላ”፤ 2002ዓ.ም፤ አሳታሚ ስንዱ መጻሕፍት)


ምንም አስተያየቶች የሉም