በልደቱ አያሌው
መፍትሄው የሚመነጨው በዶ/ር ዐቢይ አህመድ መንግሥት ተስፋ ከመቁረጥ ነው።
ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል በአማራ ማንነታቸው ምክንያት በጅምላ የጭካኔ ጭፍጨፋ ህይወታቸውን ያጡ ዜጎቻችን ጉዳይ እጅግ አስደንጋጭና አሳዛኝ ነው።
እንዲህ ዓይነቱን የጭካኔ ድርጊት ማውገዝና መቃወም ከማንኛውም ጤናማ አዕምሮ ካለው ሰብዓዊ ፍጡር የሚጠበቅ ነው።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት ሳይቋረጥ በቀጠለ ቁጥር እንደ አዲስ እየደነገጥንና እያዘንን የመቀጠላችን ምክንያት ግን የችግሩን መንስዔና መፍትሄ በውል ካለመረዳት የሚመነጭ ድክመት ነው። ጭፍጨፋ ተፈፅሞ ድንጋጤና ቁጣ በተፈጠረ ቁጥር - “ለዚህ ጭፍጨፋ ተጠያቂው ማን ነው?”፣ “እነ እከሌ ለምን ድርጊቱን አላወገዙም?” በማለት የምናነሳቸው ጥያቄዎችና “የባሰ አደጋ እንዳይመጣብን መንግሥት ባለበት ይቀጥል” በማለት የምንሰጠው አስተያየት በእርግጥም የችግሩን መንስዔና መፍትሄ በውል እንዳልተገነዘብነው የበለጠ የሚያሳይ ነው።
ስለሆነም የችግሩን መንስዔና መፍትሄ በአግባቡ ለመረዳት እንዲቻል በሚከተሉት አራት ጉዳዮች ላይ የጠራ ግንዛቤ መፍጠር ጠቃሚ ይሆናል።
1. በዜጎች ላይ እንዲህ ዓይነት ጭፍጨፋ ሲፈፀም መንግሥት በድርጊቱ ዙሪያ ቀጥተኛ ተሳትፎ ይኑረውም አይኑረውም ከተጠያቂነት አይድንም። ዜጎቹን ከሌሎች ተከታታይ ጥቃት መከላከል የማይችል መንግሥት ከተጠያቂነት አይድንም ብቻ ሳይሆን መንግሥት ሆኖ በስልጣን ላይ የመቀጠል ዕድል ሊኖረውም አይገባም።
2. የዶ/ር ዐቢይ አህመድ መንግሥት የመንግሥት የቀዳሚ-ቀዳሚ ኃላፊነት የሆነውን የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት የተሳነው ብቻ ሳይሆን በአራት ዓመት የስልጣን ቆይታው መንግሥታዊ ኃላፊነቱን አንብቦ መረዳት ያልቻለና የከሸፈ መንግሥት ስለሆነ በስልጣን ላይ እስከቀጠለ ድረስ ችግሩ የበለጠ የመባባስ እንጂ የመቆም ወይም የመቀነስ ዕድል የለውም። ለችግሩ ስለሚኖረው መፍትሄ ማሰብ የምንችለው በቅድሚያ በዶ/ር ዐቢይ መንግሥት ያለን ተስፋ ተሟጦ ሲያልቅ ነው።
3. የቀዳሚ-ቀዳሚ ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ያልቻለን ብቻ ሳይሆን ኃላፊነቱን የማወቅና የመረዳት ፍላጎት በሌለው በዚህ መንግሥት ላይ መግለጫ በማውጣት ወይም ይህን መንግሥት በማውገዝና በመቃወም የሚመጣ መፍትሄም ሆነ ለውጥ አይኖርም። መፍትሄና ለውጥ የሚመጣው የሕዝብ ፍላጎትና ውሳኔ የሚገዛው መንግሥት ለመፍጠር የሚያስችል ጠንካራና የተባበረ ትግል በማድረግ ብቻ ነው።
4. ኢትዮጵያ በዚህ ዓይነት ፈርጀ-ብዙ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ባለችበትና የዜጎች ብቻ ሳይሆን “የብሔር ብሔረሰቦች” ዋና ጠላት የሆነው “የብሔር ተኮር ፖለቲካ” የሀገሪቱ ገዢ አስተሳሰብ ሆኖ በቀጠለበት ሁኔታ ነጻ እና ፍትኃዊ የሚባል ምርጫ ማካሄድም ሆነ ቋሚ መንግሥት በቀላሉ መፍጠር አይቻልም።
በቅድሚያ ጤናማ የፖለቲካ ምህዳር እና ጠንካራ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር የሚያስችል ሁሉን-አቀፍ የሆነ የሽግግር መንግሥት ማቋቋም ለወቅቱ ችግራችን ምትክ-የለሽ አማራጭ ነው።
ከዚህ ውጪ የዶ/ር ዐቢይን መንግሥት የመፍትሄ ተስፋ አድርጎ በሚያይ ሌላ ማናቸውም ዓይነት ጥገናዊ ለውጥ ችግሩን መፍታትም ሆነ ማቃለል አይቻልም።
በአጠቃላይ - በአለፉት የአራት ዓመታት ሂደት በማያከራክር መጠን እንዳየነው የዶ/ር ዐቢይ መንግሥት የራሱንም ሆነ የሀገረ-መንግሥቱን ህልውና አፍርሶ እስከሚጨርስ ድረስ በጥፋት ላይ ጥፋትን እየጨመረ የሚሄድ እንጂ የመታረምና የመለወጥ ዕድል ያለው መንግሥት አይደለም።
መፍትሄ የማግኘት ዕድል የሚኖረን በዶ/ር ዐቢይ መንግሥት ዙሪያ ያለን የተስፋ እንጥፍጣፊ ተሟጦ ሲያልቅና ከሱ የተሻለ ስርዓት የመፍጠር ብቃትና ኃላፊነት ያለን መሆኑን አምነን ስንቀበል ነው።
ከዚህ ውጪ በወቅቱ መንግሥት ዕድሜ መራዘም ለበለጠ አደጋ የመጋለጥ እንጂ እንደ ዜጋም ሆነ እንደ ሀገር ከህልውና አደጋ የመዳን ዕድል የለንም።
የቱንም ያህል ዕድለ-ቢስ እና ደካሞች ብንሆን በማንኛውም መመዘኛ ከዶ/ር ዐቢይ መንግሥት የባሰ ደካማና ክፉ መንግሥት ሊያጋጥመን አይችልም።
አንዳንዶች በየዋህነት ወይም በአውቆአጥፊነት ሲሉ እንደሚደመጡት ኢትዮጵያ ከዶ/ር ዐቢይ መንግሥት የተሻለ መንግሥት የመፍጠር ዕድል ከሌላት በእርግጥም ሕዝቧ ከጭፍጨፋ፣ እሷም ከመፍረስ የመዳን ዕድል የላትም።
እንዲህ ዓይነት ሀገርና ሕዝብ ከሆንም መጥፋታችን የማይቀር ብቻ ሳይሆን ልንጠፋም የሚገባን ነን። የሚገባን የመሆኑና ያለመሆኑ እውነታ ደግሞ በሌሎች ደግነትና ክፋት ሳይሆን በራሳችን ምርጫ የሚወሰን ነው።ይህንን እውነታ ከመረዳት ውጪ ጭፍጨፋ በተፈፀመ ቁጥር እያዘኑ በመርሳት፣ ከዚያም እየረሱ በማዘን የሚመጣ ለውጥና መፍትሄ አይኖርም።
0 አስተያየቶች