Ticker

6/recent/ticker-posts

በሩሲያ ኤምባሲ ደጅ የተሰለፉት ኢትዮጵያዊያን ፍላጎታቸው ምን ነበር?

በሩሲያ ኤምባሲ ደጅ የተሰለፉት ኢትዮጵያዊያን ፍላጎታቸው ምን ነበር?


በሩሲያ ኤምባሲ ደጅ የተሰለፉት ኢትዮጵያዊያን ፍላጎታቸው ምን ነበር? 


"ሰው እኮ ተስፋ ሲቆርጥ [አይደለምና ሩሲያ መዝመት] ራሱንም ያጠፋል፡፡" 


አማረ ወደ ሩሲያ ኤምባሲ ያቀናው ባለፈው ቅዳሜ ነበር፡፡ ከአራት ጓደኞቹ ጋር፡፡ 


‹‹ከረፈደ ደረስኩ መሰለኝ ምዝገባ ጨርሰናል አሉኝ፡፡›› 


ለሩሲያ ለመዝመት የቆረጠው አማረ በዚህ ተስፋ አልቆረጠም፡፡ 


በድጋሚ ሰኞ ወደ ቀበና አቀና፡፡ 


የኤምባሲው ደጅ ሕዝብ ፈሶበት ደረሰ፡፡ ተሰለፈ፡፡ 


አማረ እዚህ ሰልፍ ላይ ከመሰለፉ በፊት በብዙ የሕይወት ዘርፍ ላይ ተሰልፏል፡፡ መራር ውጣ ውረዶችን አልፏል፡፡ 


ገና 27 ዓመቱ ቢሆንም በዚህ አጭር ዕድሜው ብዙ አይቷል፡፡ 


በጄ/ል አሳምነው ጽጌ ጊዜ አብሮ ሰልጥኗል፡፡ በጄ/ል ተፈራ ጊዜ ደብረዘቢጥ ግንባር ተሰልፏል፡፡ በሰሜኑ ጦርነት ተሳትፏል፡፡ ተምሮ ሥራ አጥ ሆኖ ተንከራቷል፡፡ ይህ ለ27 ዓመት ወጣት ትንሽ ነው? 


በጄ/ል አሳምነው ጽጌ ጊዜ አብሮ ሰልጥኗል፡፡ በጄ/ል ተፈራ ጊዜ ደብረዘቢጥ ግንባር ተሰልፏል፡፡ በሰሜኑ ጦርነት ተሳትፏል፡፡ ተምሮ ሥራ አጥ ሆኖ ተንከራቷል፡፡ ይህ ለ27 ዓመት ወጣት ትንሽ ነው? 


እሱም ደጋግሞ በሕይወቴ ያልሞከርኩት ነገር የለም ይላል፡፡ 


ኢኮኖሚክስ ተምሮ ተመርቆ፣ በውትድርና ተሰልፎ፣ አሁን በትንሽዬ ኢንተርኔት ቤት ፊልም ስልክ ላይ በመጫን ሥራ ኑሮውን ይገፋል፡፡ ኖሮ ግን አልገፋ ብሎታል፤ እምቢኝ አልገፋም ሲለው ወደ ሩቅ ምሥራቅ አውሮፓ አማተረ፡፡ 


ለሩሲያ የመዝመት ውሳኔ ለአማረ እንዲሁ ግብታዊ ውሳኔ ያልሆነውም ለዚሁ ነው፡፡ 


"ከጠሩኝ እዘምታለሁ" 


ሰኞ ዕለት በኤምባሲው ደጃፍ በመቶዎች ተሰልፈዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ ቢቢሲ አማረን አናግሮታል፡፡ 


የርሱ የሕይወት ውሳኔ የምን ያህል ወጣቶችን ስሜት ይወክል የሚለው ሌላ ጉዳይ ሆኖ ነገር ግን በአማረ ውስጥ የኢትዮጵያን የአሁናዊ ሁኔታ በሽንቁር ማየት የሚያስችል ይመስላል፡፡ 


ሰኞ ዕለት ተመልሶ ወደ ኤምባሲው የሄደው አማረ ምን ገጠመው? 


‹‹…አታሼ የሚባል ሰውዬ ብቅ ብሎ 'ዶክመንታችሁን ትታችሁ ሂዱ፤ አዲስ ነገር ካለ እንነግራችኋለን' ብሎን ገባ፡፡›› 


አማረ ያን ሰው በሩቁ አይቶታል፡፡ ኋላ ላይ የወጣው የኤምባሲው ‹የእኔ የለሁበትም› ማስተባበያ ያልተዋጠለትም ለዚሁ ነው፡፡ 


‹‹እርግጥ ረዥም ሰልፍ ስለነበረና ኋላ ስለነበርኩ ሰውዬው ያለውን በጆሮዬ አልሰማሁም፡፡ የረባ መረጃ የሚሰጥም ሰው አልነበረም፡፡›› 


በመጨረሻ አማረና ጓደኞቹ ሰነዳቸውን አሰባስበው ለሰውየው ሰጥተው ሄዱ፡፡ 


የነሱ ማስረጃ የትምህርትም የውትድርናም ነው፡፡ በሰልፍ ላይ ያሉ ወጣቶች ግን አንዳንዶቹ የውትድርና ልምድ እንደሚያስፈልግ ሲያውቁ አዝነው ጥለው ሄደዋል፡፡ 


አንዳንዶቹ ደግሞ ከጠሩ ይጥሩን ካልጠሩንም የራሳቸው ጉዳይ በሚል ማስረጃቸውን ሰጥተዋል፡፡ 


የ2ሺህ ዶላር ወሬ 


ለመሆኑ አማረ ዜናውን እንዴት ሰማ? 


በሩሲያ ኤምባሲ በድንገት በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች በአንድ ጊዜ እንዴት ሊገኙ ቻሉ የሚለው ላለፉት ቀናት መነጋገሪያ ነበር፡፡ 


እነዚያ ወጣቶች የመረጃቸው ምንጭ ምንድነው? 


አማረ ወሬውን የሰማው ከሰዎች ነው፡፡ 


‹‹በፊት ወታደር ቤት አውቃቸው የነበሩ ሰዎች ናቸው ደውለው የነገሩኝ›› ይላል፡፡ 


ከነርሱ ከመስማቱ በፊት ግን በማኅበራዊ ሚዲያም ስለነገሩ በገደምዳሜ ሰምቷል፡፡ 


"የሁለት ዓመት ደመወዝ ቀድሞ እንደሚሰጥ ነበር የሰማሁት፡፡" ይላል፡፡ 


ነገሩ ዕውነት ሳይሆን አይቀርም ብሎ እንዲያስብ ያደረገው ከዚህ ቀደም በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የተሰራጩ ተያያዥ ዜናዎች ናቸው፡፡



የምዕራብ አገራት የግል የደኅንነት ተቋሞች ለዩክሬን የሚዋጉ ቅጥር የውጭ ዜጎችን እየመለመሉ እንደሆነ የወጣው ዜና በተለይ የብዙዎችን ልብ ሳያሸፍት አልቀረም፡፡ 


በተለይ በቀን 2ሺህ ዶላር እንደሚከፈል የምታትተው ርዕሰ ዜና፡፡ 


‹‹ያን መረጃ ሳነብ ምነው ይሄ ነገር ወደ ኢትዮጵያም በመጣ የሚል ሐሳብ ውልብ አለብኝ፡፡ ከጓደኞቼ ጋር እናወራበትም ነበር፡፡›› 


በአዲስ አበባ የዩክሬን ኤምባሲ ይህን ሰልፍ ተከትሎ በኢትዮጵያ የሩሲያ ኤምባሲ ወጣቶችን ለውትድርና እየመለመለ ነው የሚል ክስ አቅርቦ መግለጫ አውጥቷል፡፡ 


ምናልባት የዩክሬን ኤምባሲ ልብ ያላለው እነ አማረ የቀበና ሰልፍ ቢረዝምባቸው ቦሌ ዩክሬን ኤምባሲ መጥተው ቢሰለፉም ግድ እንደማይሰጣቸው ነው፡፡ 


‹‹ያው በተለምዶ ሩሲያ ናት የኢትዮጵያ ወዳጅ አገር እንላለን፤…እኔ በዚህ ውትድርና ዘርፍ ከማንኛውም አካል ጋር ለመሥራት ዝግጁ ነን፡፡ ዩክሬን፣ ራሺያ ለኔ ያው ነው፡፡›› ይላል፡፡ 


የሩሲያ ኤምባሲ ለምን አስተባበለ? 


አማረ ይህን ክስተት ተከትሎ የሩሲያ ኤምባሲ ስላወጣው ማስተባበያ ሲሰማ አልተዋጠለትም፡፡ 


‹‹በእርግጥ ማስታወቂያ አላወጡ ይሆናል፡፡ ነገር ግን እየመለመሉ ባይሆን መረጃዎቻችንን ለምን ተቀበሉን?››፡፡ ሲል ቁልፍ ጥያቄ ይጠይቃል፡፡ 


ታዲያ ኤምባሲው ለምን አስተባባለ? 


ኤምባሲው ማስተባበል የፈለገው ምናልባት በስፍራው ግርግር እንዳይፈጠር ስለፈለገ፣ እየመለመሉ ነው እንዲባል ስላልተፈለገ ወይም ትኩረት ላለመሳብ ይሆናል ብሎም ይገምታል፡፡ 


የእርግጠኝነቱን መጠን ሲገልጥም ‹‹መረጃችንን የሰበሰበውን ሰውዬ አሁን መንገድ ላይ ባየው እለየዋለሁ›› እስከማለት ይደርሳል፡፡ 


"ለአገር የምትሞቺው እኮ የምትሞቺላት አገር ስትኖርሽ ነው" 


ለብዙዎች ጥያቄ ሆኖ የሰነበተው ጉዳይ እንዴት አንድ ኢትዮጵያዊ ሩሲያ ድረስ ለመዝመት ወዶና ፈቅዶ ኤምባሲ ደጅ ይሰለፋል የሚለው ነው፡፡ 


መቼስ ጠንካራ ገፊ ምክንያት መኖር አለበት፡፡ 


በእርግጥ ነገሩ በጥሬው የኢኮኖሚ ጥያቄ ብቻ ነው? 


ምስቅልቅሎሻዊ አሁናዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ መገለጫ ነው? ወይስ ሌላ? 


ለአማረ የውሳኔው ምንጭና ጥሬ ምክንያት ተስፋ ማጣት ነው፡፡ እሱም ነገሩን በአጭሩ ሲያስቀምጠው እንዲህ ይላል፡-"ሰው እኮ ተስፋ ሲቆርጥ [አይደለምና ሩሲያ መዝመት] ራሱንም ያጠፋል፡፡" 


ሌሎች ምክንያቶች የሉም ማለት ግን አይደለም፡፡ 


የኢትዮጵያ የክፉ ጊዜ አጋር ለሚሏት ሩሲያ ውለታ ለመክፈል ነው የምንዘምተው ያሉ አሉ፡፡ 


በምዕራብ አገራትና የዲሞክራሲ ግብዝነታቸው ላይ የተሠራ ሰፊ የሚዲያ ዘመቻ ውጤትም ሊሆን ይችላል፡፡ በመላምት ደረጃ፡፡ 


ለነዚህ መላምቶች መነሻ የሚሆኑ መረጃዎችን ቃርመናል፡፡ 


ለምሳሌ ‹የኔታ› በሚባል ከፍተኛ ተመልካች ያለው አንድ የዩትዩብ ሚዲያ የቀረቡ ሰው ነበሩ፡፡ 


መቶ አለቃ በላይ ግደይ ይባላሉ፡፡ ሚዲያው በኤምባሲው አቅራቢያ ቃለ ምልልስ ሲያደርግላቸው ይታያል፡፡ 


ለምን ወደ ኤምባሲው እንደመጡ ሲጠየቁ ለሥራ እንዳልሆነ አስረግጠዋል፤ ‹‹እኔ ሥራ አለኝ፡፡ ዶላር ለማግኘት አይደለም ለሩሲያ የምዘምተው፡፡›› ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ 


ሁነኛ ምክንያታቸውን ሲያብራሩም፣ የዓለም ብዙ አገራት ቀውሶች መነሻ ምዕራብ አገራት እንደሆኑ ጠቅሰው ሩሲያ ግን በዚህ ጣልቃ ገብነት እንደሌለችበት አስምረው ያሞካሽዋታል፡፡ 


‹‹ራሺያ የኢትዮጵያ ወዳጅ ናት፡፡ ያቺ አገር ከኔ የምትፈልገው ነገር ካለ ለመሰለፍ ዝግጁ በመሆኔ ነው ወደ ኤምባሲው የመጣሁት›› ይላሉ፡፡ 


እኚህ መቶ አለቃ የቀድሞ ጦር አባል እንደሆኑም ጠቅሰዋል፡፡ 

አናዱሉ የተባለ የቱርክ ዜና አውታር የጠቀሳቸውና በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት መሳተፋቸውን የገለጹ አስር አለቃ ታረቀኝ ዋሴ ባለትዳርና የልጆች አባት ናቸው፡፡ 


እሳቸው ውሳኔያቸው ሁለት ገጽታ አለው፡፡ 


ለሩሲያ ፍቅር እንዳላቸውና ጥሩ ገቢ የሚያስገኝ ከሆነ ለመዋጋት ወደ ኋላ እንደማይሉ ተናግረዋል፡፡ 


በሰልፉ ላይ የነበሩ በርካታዎች የውትድርና ልምድ ያላቸው መሆኑ የተዘገበ ሲሆን፤ ተመርቀው ሥራ ያላገኙ ወጣቶችም በስፋት እንደነበሩ አማረ ታዝቧል፡፡ 


"ስትገድይው የመንግሥት ኃይል ነው፤ ከገደለሽ ደግሞ የታጠቀ ኃይል ነው ይሉሻል፡፡" 


አማረ ስለምን በብዙ ማይል ለምትገኝ አገር ለመሞት እንደወሰነ ሲጠየቅ ያለፈ ቁስሉን በማስታወስ ለማስረዳት ይሞክራል፡፡ 


‹‹እናቴን አሳፍሪያት አላውቅም፤ ተምሬ ግን መና ቀረሁ፡፡ ትርጉም ያለው መስሎኝ ለአገሬ ተሰለፍኩ፡፡ ብቻ ተይው›› 


ይህ ስሜት የርሱ ብቻ ሳይሆን ኤምባሲው ደጅ የተሰለፉ ጓደኞቹም የሚጋሩት እንደሆነ ያብራራል፡፡ 


"እንኳን አሁን፣ ዐቢይ ለከዳን ትርጉም ለሌለው ጦርነትም ተዋድቀናል የሚል ስሜት ነበር ሰልፉ ላይ የነበረው የጓደኞቼ ስሜት፤ የኔም ስሜት ያ ነበር፡፡" 


አማረ የአማራ ልዩ ኃይል ነበር፡፡ ልዩ ኃይል ከመሆኑ በፊት ደግሞ በኢኮኖሚክስ ተመርቋል፡፡ ከዚያ በኋላ አዲስ አበባ ወረዳ አካባቢ ሥራ ሞካክሯል፡፡ ሟቹ ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ይመሩት በነበረው ልዩ ኃይል የ8 ወራት ስልጠና ወስዷል፡፡ 


እሱ ብቻ ሳይሆን አብረውት ኤምባሲ የነበሩት የልዩ ኃይል አባላትም በተመሳሳይ ሕይወት ነው ያለፉት፡፡ 


‹‹ከ8 ወር ስልጠና በኋላ መጨረሻ ላይ ነገሩ ሲበላሽ ከልዩ ኃይል ጥለን ወጣን፡፡ ከዚያ በኋላ ብዙ ነገር ሞክረናል፡፡›› ይላል፡፡ 


ይህ በየቀኑ እያበደ ያለው የኑሮ ውድነት ከሥራ ማጣት ጋር ተዳምሮ ያለፈውን ሕይወቱን እንዲፈትሽ ያደረገው ይመስላል፡፡ 


‹‹የኑሮ ጣዕምን ጨርሶ የምታጪበት ጊዜ አለ፡፡ በቃ ያኔ ነው ለራሺያ ለመዋጋት የወሰንኩት፡፡" ይላል፡፡ 


ኖሮ እንዴትስ ጣዕሙን ቢያጣ ለባዕድ አገር ከመዝመት መለስ ያሉ ብዙ አማራጮች የሉም? 


አማረ እነዚህን አማራጮች ሞክሪያቸዋለሁም አይቻቸዋለሁ የሚለው ስሜታዊ በመሆንም ጭምር ነው፡፡ 


"ዩኒቨርስቲ አንድ ላይ ቁጭ ብለን፣ አንድ ዶርም አድረን ከተማርን የትግራይ ጓደኞቼ ጋር ገጥሜ ነው የመጣሁት፡፡ ወይ እነሱ ሞተዋል፡፡ ወይ ገድለዋል፡፡ ይሄ ይሄን ስታዪ ያስጠላል፡፡ የጓደኞቻችንን ሬሳ በየመንገዱ ጥለን በወጉ እንኳን ሳንቀብር ነበር የምንዋጋው፡፡ …በጦር ሜዳ ተመትቶ ለመሞት ሲያጣጥር ያየሁት የትግራይ ልጅ እስከዛሬ ከአእምሮዬ አልጠፋም፡፡ እሱም በዚያ በኩል በፖለቲካ ተታሎ ነው፤ እኛም በዚህ በኩል…፡፡" 


አማረ ያሳለፈው ሕይወት ምንስ መራር ቢሆን በሺ ማይል ርቀት ላለ አገር ተዋግቶ ለመሞት የሚያደርስ ምን ተገኝቶ ነው፡፡ ከሞቱ አይቀርስ ለአገር መሞት አይሻልም? 


ለዚህ ዘርዘር ያለ ምላሽ ለመስጠት ይንደረደራል አማረ፤ በታከተ ስሜት፡፡ 


‹‹ሰው ለሁለት ነገር ይዋጋል፡፡ አንዱ ስለ አገር ፍቅር ነው፡፡ አባቶቻችን ጫማ ሳይኖራቸው ተዋግተዋል፡፡እኛም እኮ መስሎን ተዋግተናል፡፡ ኢትዮጵያ ልትፈርስ ነው ብለውን አዋግተውናል፡፡›› 


‹‹ወታደር መሆን ትርጉም የሚኖረው የምታድኚው አባት፣ የምታድኚው እናት፣ የምታድኚው አገር ሲኖር ነው፡፡ አገር ስልሽ የምታኖርሽ አገር ማለቴ ነው፡፡አንድ ሰው ተራው ሲደርስው የሚዘውራት አገር ማለቴ አይደለም፡፡›› 


‹‹ሁለተኛው ውትድርና ዋጋ ሲያስገኝ ነው ትርጉም የሚሰጠው፡፡ አባቶቻችን ኮሪያ ዘምተዋል እኮ፡፡የሞተው ሞቶ የዳነው ባለ ክብር ባለ ርስት ሆኗል፡፡ አገርሽን አስጠርተሸ ተመልሰሽ ላንቺም ክብር አግኝተሸ ስትኖሪ ውትድርና ትርጉም አለው፡፡›› 


‹‹አሁን ግን ከፋፍለውናል፤ ሞት አልቀረም፤ መዋጋታችን አልቀረም፡፡ ስትገድይው የመንግሥት ኃይል ነው፤ ከገደለሽ ደግሞ የታጠቀ ኃይል ነው፡፡ ሸኔ ነው፡፡ ይሉሻል፡፡ ስለዚህ ሞት የማይቀር ከሆነ ለቤተሰብ መትረፍ ይሻላል ብዬ ነው፡፡ ለእናቴ አሳልፌላት ብሞት ምናለበት ብዬ ነው፡፡ እንጂማ ገና የሄድሽ ዕለትም ልትሞቺ ትችያለሽ እኮ፡፡" 


አማረ አሁን ከሩሲያ ኤምባሲ ከዛሬ ነገ ጥሪ ይደርሰኛል ብሎ በተስፋ ይጠብቃል፡፡ እስከዚያ በኢኮኖሚክስ ዲግሪ ተመርቆ ለደንበኞች በስልካቸው ፊልም ይጭናል፡፡ የፍቅር ፊልም፣ የጦርነት ፊልም…፡፡

አስተያየት ይለጥፉ

0 አስተያየቶች