Ticker

6/recent/ticker-posts

ህወሓት ተዋጊዎቼን ከዓፋር ክልል ኤሬብቲ አካባቢ አስወጥቻለሁ አለ

የትግራይ ሰራዊት ሰኔ ወር መቐለ ሲገባ/ምስል ኤ ኤፍ ፒ
የትግራይ ሰራዊት ሰኔ ወር መቐለ ሲገባ/ምስል ኤ ኤፍ ፒ



ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ጦርነት ውስጥ የገባው ህወሓት በዓፋር ክልል ኤሬብቲ ተብሎ የሚጠራ ስፍራን ተቆጣጥረው የነበሩ ተዋጊዎቼ አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ አድርጊያለሁ አለ።



ህወሓት ሠራዊቱን ኤሬብቲ ተብሎ ከሚጠራው ስፍራ ለማስወጣት ከውሳኔ የደረሰው ለሰብአዊነት ሲባል የተደረሰው ስምምነት ተከብሮ ያልተገደብ ሰብአዊ እርዳት ትግራይ እንዲደርስ ነው ብሏል።



ሚያዚያ 5 ቀን 2014 ዓ.ም በክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ በተላለፈው መግለጫ፤ "የትግራይ መንግሥት የሰላም ውይይቱን ለማሳለጥ በተለይም ለሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ሚያዚያ 4 ቀን 2014 ዓ. ም የትግራይ ሠራዊት ተቆጣጥሮት ከነበረው ኤሬብቲ ተብሎ ከሚጠራው የዓፋር አካባቢ ሠራዊቱ እንዲነሳ ተደርጓል" ብሏል።



ህወሓት ይዟቸው ከነበራቸው የዓፋር ክልል አካባቢዎች ለቅቆ ስለመውጣቱ ቢቢሲ ከአፋር ክልል መንግሥት ለማረጋገጥ ያደረግኩት ጥረት ስልክ ባለመነሳቱ ሳይሳካልኝ ቀርቷል ሲል አስነብቧል።



የህወሓት ኃይሎች በዓፋር ክልል ዞን ሁለት የሚገኙ ወረዳዎችን በቁጥጥራቸው ስር ያዋሉት በጥር ወር አጋማሽ ላይ ነበር።



ከዚህ ቀደም የአፋር ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አሕመድ ኻሎይታ የህወሓት ኃይሎች በአፋር ክልል ዞን ሁለት ውስጥ የሚገኙ አምስት ወረዳዎችን መቆጣጠራቸውን ተናግረው ነበር።



በኪልበቲ ረሱ ዞን በህወሓት ቁጥጥር ሥር ገብተዋል ተብለው ከነበሩት 5 ወረዳዎች መካከል አብዓላ፣ መጋሌ፣ ኤሬብቲ እና በራሕለ ይገኙባቸዋል።



ህወሓት ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ ሠራዊቴን አስወጥቻለሁ ያለው ኤሬብቲ ተብሎ ከሚጠራው ዓፋር ውስጥ ከሚገኝ ስፍራ ነው።



ህወሓት ከአፋር ክልል ሙሉ በሙሉ ስለመውጣቱ ማረጋገጥ አልተቻለም።

አስተያየት ይለጥፉ

0 አስተያየቶች