ሰሞኑን በሕግ ጥላ ሥር እንዲውሉ የተደረጉ ጋዜጠኞች የሚገኙበት ሁኔታ በቤተሰቦቻቸው እንዲታወቅ አለመደረጉን እንደሚያወግዝ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ማኅበር ተናገረ።
ማኅበሩ ኢትዮጵያ የምትገኝበትን ወቅታዊ ሁኔታ እንደሚገነዘብ በመግለጥ፤ ጋዜጠኞች በትክክል ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ለእሥር መዳረጋቸው፤ የጋዜጠኝነት ትግበራ ነፃነት ላይ ጥቁር ጥላ እንዳያጠላበት ሥጋት ፈጥሯል ብሏል።
ማኅበሩ ጋዜጠኞቹ ፍትሕ እንዲያገኙ፣ የሕግ ድጋፍ የማግኘት መብታቸውም እንዲጠበቅና ቤተሰቦቻቸውም ጋዜጠኞቹን የመጠየቅ መብታቸው እንዲከበር ጠይቋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎች ማኅበር በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የውጭ መገናኛ ብዙኃን የተዛቡ እና ሚዛናዊነት የጎደላቸው ዘገባዎች እየተሰራጩ መሆኑን ተመልክቻለሁ ያለው ማኅበሩ መገናኛ አውታሮቹ ከዚህ መሰሉ ዘገባ እንዲወጡም ጠይቋል። በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር እንዲያድግ፣ ሞያውም በመርኁ መሰረት እንዲተገበር ዘርፉን የተመለከተ አገር አቀፍ ውይይት እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል።
ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመታት በፊት የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀንን አዲስ አበባ ውስጥ አክብራ የነበረ ሲሆን፤ በወቅቱ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (CPJ) ኢትዮጵያን ለመጀመርያ ጊዜ ጋዜጠኞች ያልታሰሩባት አገር በሚል ጠቅሷት ነበር። የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪ ድርጅቱ ከቀናት በፊት ባወጣው የ2021 ዓ.ም ዘገባው ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማሰር ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት ሁለተኛ ናት ብሏል።
0 አስተያየቶች