Latest

ads header

ዜና

"የተመለከትነው ቪድዮ በጣም የሚረብሽና የሚያስደነግጥ ነው" - ኢሰመኮ



የአዲስ  አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ፥በአንዲት ግለሰብ ላይ ድብደባ የፈፀሙ የፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር ዉለዉ ምርመራ እየተጠራባቸው መሆኑን አስታውቋል። 



በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2  ልዩ ቦታው ሚካኤል አደባባይ አካባቢ መስከረም 21 ቀን 2014 ዓ/ም  ከቀኑ  5፡00 ሰዓት ም/ኢ/ር  ጃፋር አሊ እና ኮንስታብል መስፍን በተለ የተባሉ  የቆሬ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ አባላት አንዲትን ግለሰብ በአስነዋሪ ሁኔታ በመደብደባቸው  በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጠራ እንደሚገኝ ፖሊስ ገልጿል። 


"ህዝብን በሰብአዊነት ማገልገል የአዲስ አበባ  ፖሊስ መርህ መሆኑ እየታወቀ ነገር ግን አንዳንድ አመራሮችና አባላት ይህን  መርህ በመተላለፍ  የሚፈፅሙት ህገ-ወጥ ድርጊት ተቋሙ አይታገስም" ያለው ፖሊስ በ2013 የበጀት ዓመት በልዩ ልዩ ጥፋት ላይ የተገኙ 171 የፖሊስ አመራሮችና አባላት ከሰራዊቱ እንዲሰናበቱ  መደረጉን ገልጿል። 


ከስራ ከተሰናበቱት 29ኙ ከሰብአዊ መብት ጥስት ጋር በተያያዘ መሆኑን የአዲስ  አበባ  ፖሊስ  አሳውቋል። 


ፖሊስ ህግን በመተላለፍ ጥፋት በሚፈፁም አባላትና አመራሮች ላይ የሚወስደውን እርምጃ  አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቆ ህብረተሰቡ  እንዲህ ዓይነት ከፖሊስ የሙያ  ስነ- ምግባር ውጪ የሆኑ ድርጊቶች በሚፈፀሙበት ወቅት በፍጥነት ጥቆማ እንዲያደርግ ገልጿል። 

ተበዳይዋን የደበደቡ የፖሊስ አባላት


ግለሰቧን በደበደቡ የፖሊስ አባላት ላይ አስፈላጊውን እርምጃ  ተወስዶ  ውጤቱን ለህዝብ  አሳውቃለሁ ብሏል አዲስ  አበባ  ፖሊስ።



ድብደባውን ተከትሎ ምላሽ የሰጠው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በበኩሉ ድርጊቱ አስደንግጦኛል ብሏል። 


በሁለቱም የፖሊስ አባላት ድብደባ ሲፈፀምባት የነበረችው እናት በልመና የምትተዳደር እንደሆነችና አጠገቧ የነበረችውም ልጇ እንደነበረች ተረጋግጧል። 


የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ(ዶ/ር) ሲናገሩ "የተመለከትነው ቪድዮ በጣም የሚረብሽና የሚያስደነግጥ ነው" ብለዋል። 


ኮሚሽኑ የተሟላ መረጃ ለማግኘት እየሰራ መሆኑን እና ክትትሉም እንደሚቀጥል አስረድተዋል።


"በርካታ ዜጎቻችን ልብ የሚሰብር የቪዲዮ ምስል በማህበራዊ ሚዲያ ሲቀባበሉ ተመልክተናል" ያሉት ደግሞ  የሰላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል ናቸው። 


ሚኒስትሯ "የጀመርነው ተቋማዊ ለውጥ ሀላፊነትን ከነተጠያቂነቱ አጣምሮ የያዘ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ ከፌዴራል ፓሊስ አመራሮች ጋር መረጃ ተለዋዉጠናል" ብለዋል። 


ወ/ሮ ሙፈሪሃት ዜጎች ለሰብዓዊ መብት መከበር እንዲህ አይነት ህገወጥ  ተግባራትን በመከታተልና በማጋለጥ ረገድ ማህበራዊ ሚዲያን አዎንታዊ ለሆነ ተግባር ማዋል መቻላቸው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባልም ብለዋል።



ምንም አስተያየቶች የሉም