Ticker

6/recent/ticker-posts

በአዲስ አበባ የታሰሩ የትግራይ ተወላጆች ቤተሰቦች ስጋትና የመንግሥት ምላሽ




የ72 ዓመቱ አዛውንት አቦይ ተኽለ ኪዳን በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ከ40 ዓመታት በላይ ኖረዋል። ከበኩር ልጃቸው ውጪ ያሉት ስድስት ልጆቻቸው ተወልደው ያደጉትም አዲስ አበባ ነው። 


ከአስር ዓመት በፊት ጡረታ ወጥተው በግል የትራንስፖርት ሥራ ላይ ተሰማርተው ነበር። እድሜያቸው እየገፋ ሲመጣ ደግሞ ከትዳር አጋራቸው ጋር ቆርበው ብዙ ጊዜያቸውንም ቤታቸው እና ቤተ ክርስቲያን እንደሚያሳልፉ ቤተሰቦቻቸው ይናገራሉ። 


ከሳምንት በፊት ግን ከአስር በላይ የሚሆኑ የፖሊስ አባላት ቤታቸው ድረስ በመምጣት እንደሚፈለጉ ገልጸው "ቤቱን ፈትሸው ምንም ነገር ሳያገኙ፣ እያንገላቱ ወሰዷቸው" ሲል ልጃቸው ገልጿል። 


"በተወለድኩባት እና አገሬ በምላት ከተማ እንደዚህ አይነት ነገር አያለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም" ይላል ልጃቸው። 



ከተጀመረ አንድ ዓመት ያስቆጠረው ጦርነት ከትግራይ ክልል ወጥቶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ተስፋፍቶ መቀጠሉን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ለስድስት ወራት የሚቆይ አገር አቀፍ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል። 


አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዜጎች መታወቂያ ይዘው እንዲንቀሳቀሱና በፀጥታ ኃይሎች ሲጠየቁ እንዲያቀርቡ ያስገድዳል። 




አዋጁ መተግበር ከጀመረ በኋላ በተለይ በአዲስ አበባ የሚኖሩ በርካታ የትግራይ ተወላጆች ለእስር መዳረጋቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ አመልክቷል። 


ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና የመብት ተቆርቋሪዎች እስሩ ማንነት ላይ ያነጣጠረ ነው ቢሉም የአዲስ አበባ ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካው ፈንታ ''እየተወሰደ ያለው እርምጃ ከሽብር ቡድን ጋር ግንኙነት ባላቸው ላይ ነው፣ በዚህም እየተያዙ ያሉት የትግራይ ተወላጆች ብቻ አይደሉ" ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል። 


በእስር ሂደቱ ውስጥ ታዋቂ ሰዎችና የተለያዩ ተቋማት ኃላፊ የሆኑ የትግራይ ተወላጆች መታሰራቸውን ሮይተርስ ባለፈው ሳምንት አመልክቶ፤ ከእነዚህም መካከል ዳንኤል ተኽለ የተባሉ የአንበሳ ባንክ ፕሬዝዳንትና አምስት ሠራተኞች ታሰረው መለቀቃቸውን ዘግቧል። 


የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ እንዳሉት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ተያይዞ "ለአሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ ድጋፍ በማድረግ የተጠረጠሩ ግለሰቦች እንጂ ብሔርን መሰረት ያደረገ እስራት አልተፈጸመም" ማለታቸው ተዘግቧል። 


ሚኒስትሩ ጨምረውም በአዲስ አበባ ከተማ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የትግራይ ተወላጆ እንደሚኖሩ እንደሚገመት አመለክተው "የታሰሩት ከአንድ ሺህ የማይበልጡ ናቸው" ብለዋል። 


አገልግል ሚዲያ ያነጋገራቸው በ'ብሔር' ተጋሩ ያልሆኑ የታሳሪ ቤተሰቦች "በስም ስህተት ለእስር ተዳርገው ብሔራቸው የትግራይ ተወላጆች አለመሆናቸው ሲጣራ ከእስር የተፈቱ ሰዎች አሉ፤ የትግራይ ተወላጆች ግን ሳያጠፉ አሁንም እስር ላይ ናቸው።" ብለዋል። 


ቢቢሲ አናገርኩት ያለው አዲስ አበባ ተወልዶ ያደገ ወጣት ከ10 ዓመት በላይ በፌደራል ፖሊስ ያገለገለች እና በሰንዳፋ የፌደራል ፖሊስ ኮሌጅ መምህር የነበረች አክስቱ እንደተያዘች ይገልጻል። 


"ከሁለት ወር በፊት እሷ እና ሌሎች የትግራይ ተወላጆች 'ለስልጠና እንፈልጋችኋለን' ብለው ወስደው ለ20 ቀናት ሰንዳፋ በሚገኝ የስልጠና ማዕከል ካቆይዋቸው በኋላ ወደ ጦላይ ወሰዷቸው" ይላል። 


ትዕግስቲ [ስሟ ተቀይሯል] ባለ ትዳር እና የሁለት ልጆች እናት ናት። የሰባት እና የአራት ዓመት ልጆቿ' 'እናታችን' እያሉ እያለቀሱ ነው'' በማለት ህጻናት ልጆቿ እያስቸገሩ መሆናቸውን ይናገራል። 


የትግራዩ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ በመከላከያ፣በ ፌደራል ፖሊስና በደኅንነት ተቋም ውስጥ ሲሰሩ የነበሩ የትግራይ ተወላጆች ሥራ እንዲያቆሙ እንደተደረጉና አብዛኞቹ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለአንድ አመት ያህል በተለያዩ እስር ቤቶች  ታስረው እንደሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ተናግረዋል። 


በተለይ በመከላከያ ሠራዊት ስር ለረጅም ዓመታት ተቀጥረው ይሰሩ የነበሩ የትግራይ ተወላጅ የሠራዊቱ አባላት ጦርነቱ በጀመረ ማግስት ታስረው አብዛኞቹ እስካሁን ለፍርድ አልቀረቡም። 


"ከህወሓት ጋር ግንኙነት አላቸው" የሚል ክስ የቀረበባቸው ደግሞ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ቀርበውም በተወሰኑት ላይ እስር ተፈርዶባቸዋል።



በመንግሥት ሆስፒታል የልብ ህክምና ዶክተር ሆኖ የሚሰራው ወንድሙ የታጠቁ ፖሊሶች እና ሲቪል የለበሱ የደኅንነት ሰዎች ሥራ ቦታው መጥተው እንደወሰዱት የሚናገረው ለደኅንነቱ ሲል ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገው ግለሰብ ወንድሙ "ከማንነቱ በስተቀር ምንም አይነት ጥፋት የለበትም" ብሎ ያምናል። 


''ከጁንታ ጋር ግንኙነት እንዳለህ ጠርጥረናል'' ብለው እያንገላቱ መጀመሪያ ወደ ገርጂ ቆይተው ወደ ለገሀር ፖሊስ ጣቢያ እንደወሰዱት ይናገራል። 


"አንድ ጊዜ ብቻ ነው ያናገርነው" የሚለው የታሳሪው ወንድም፣ ፖሊስ በቅርብ ሆኖ ስለሚያዳምጥ ''ደህና ነኝ'' ከማለት ውጪ ስለተፈጠረው ነገር መናገር እንዳልቻለ ገልጿል። 


የሐኪሙ ወንድም የተያዘበት እና አዛውንት አባቱ የታሰሩበት አርቲስት ለማስፈታት ገንዘብ የሚፈልጉ እንዳሉ፣ ከፍለው የተፈቱ እንዲሁም ከፍተኛ ከንዘብ የተጠየቁ ሰዎች እንደሚያውቁ ገልጸዋል። 


ገንዘብ ከከፈሉ በኋላ ከእስር ተፈትተው በድጋሚ የታሰሩ ሰዎች መኖራቸውን የትግራይ ተወላጅ ያልሆኑ አገልግል ሚዲያ ያነጋገራቸው የታሳሪ ቤተሰቦች ገልፀዋል። 


የአዲስ አበባ ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካው ፈንታ ከገንዘብ ክፍያው ጋር በተያያዘ ምላሽ ሲሰጡ በማስፈራራት እንዲሁም የታሰሩ ሰዎችን ለማስለቀቅ ገንዘብ ለመቀበል የሞከሩ አምስት የፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገ ነው ብለዋል። 


ይህ ክስተት በጥቂት ግለሰቦች የሚፈጸም ሕገወጥ ድርጊት በመሆኑ የአጠቃላዩን የፖሊስ አባል የሚወክል አይደለም ብለዋል። እንዲህ አይነቱን ተግባር "እንደ ተራ ወንጀል አናየውም። አገር እንደመክዳት ነው የምንቆጥረው" ሲሉም ገልፀዋል።



የትግራይ ተወላጅ የሆኑ አንዳንዶቹም የብሔሩ ተወላጅ መሆናቸው እንኳን የማያውቁ ቤተሰቦች ከነልጆቻቸው በጅምላ መታሰራቸው እና መጉላላታቸውን ጎረቤቶቻቸው ይገልጻሉ። 


የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጠው መግለጫ በከተማዋ እየተካሄደ ያለው እስራት እናቶች እና ህጻናት እንደሚጨምር እና ማንነት መሰረት ያደረገ እንድሚመስል ጠቅሷል። 


ቢቢሲ ያነጋራቸው ሰዎች ከታሰሩ ቤተሰቦቻቸው እስካሁን ፍርድ ቤት የቀረበ እንደሌለ ይናገራሉ። 


እስር ቤቶች በመሙላታቸው ብዙ ሰዎች በትምህርት ቤቶች ቅጥር ግቢ እና መጋዝኖች ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ እንደሚገኙ የዓይን እማኞች ገልጸዋል። 


ብዙ ሰዎች ቤተሰቦቻቸው የት እንደታሰሩ የማያውቁ ሲሆን አንዳንዶቹ አፋር ክልል ወደ ሚገኘው አዋሽ አርባና ኦሮሚያ ክልል ወደ  ሚገኘው ሰንዳፋ መወሰዳቸውን ተናግረዋል። 


ኮማንደር ፋሲካው እስካሁን አዲስ አበባ ውስጥ ምን ያህል ሰው አንደታሰረ መረጃ እንደሌላቸው ጠቅሰው አንዳንድ ሰዎች ከጥቂት ቀናት በኋላ መለቀቃቸውን ገልጸዋል። 


የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በአንድ ክፍለ ከተማ ከሰባት መቶ በላይ ሰዎች መታሰራቸውን ሲገልፅ፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ደግሞ የታሳሪዎቹ ቁጥር ቢያንስ አንድ ሺህ እንደሚሆን አመልክቷል። 


እስሩ በአዲስ አበባ ውስጥ ብቻ የሚፈጸም አለመሆኑን ከተለያዩ አካባቢዎች የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። 


በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን እስሩ እንዳሳሰበው በሰጠው መግለጫ ላይ በተለያዩ ስፍራዎች እየተፈጸመ መሆኑን አመክልቷል። 


የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ሊዝ ትሮሰል የትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠሩ እስሮች መበራከታቸው ተቋሙን እንዳሳሰበውና እስሩ በአዲስ አበባ፣ በጎንደር፣ በባሕር ዳር እና በሌሎች አካባቢዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ ፖሊስ ፍተሻ እያደረገ እና በርካታ ሰዎችን እያሰረ ነው ብለዋል። 


የፌደራል ፖሊስ አባል የነበረችው ታሳሪ የአድዋ ከተማ ተወላጅ ናት። 


የአንድ ልጅ አባት የሆነው ዶክተር ግን አዲስ አበባ ተወልዶ ማደጉን ዘመዱ ይናገራል። 


"ለረጅም ጊዜ እዚህ ከተማ ውስጥ ነው የኖርነው፤ እርግጥ ትግራይ ውስጥም ቤተሰቦች አሉን። ተጋሩ መሆናችንም እናውቃለን፤ ጎረቤቶቻችንም ያውቃሉ። ማንነታችን ደብቀን አልኖርንም። እንዲህ አይነት ነገር ይመጣል ብለንም አስበን አናውቅም" ይላል። 


በተጨማሪ "ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ባለው አንድ ዓመት ትግራይና ተጋሩን በተመለከተ የሚነገሩ ነገሮች ደስ አይሉም። ከቅርብ ጓደኞቼ የደረሰብኝ ምንም ነገር የለም። ነገር ግን ብዙ የተንገላቱ ቤተሰቦች አሉኝ" በማለት የተፈጠረበትን መጥፎ ስሜት ይገልጻል። 


አብዛኞቹ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የታሳሪዎች ቤተሰቦች ይህ አስቸጋሪ ሁኔታ "እንደምንም ያልፋል" ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።

አስተያየት ይለጥፉ

0 አስተያየቶች