Ticker

6/recent/ticker-posts

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ጦር ግንባር እንደሚዘምቱ ገለፁ



ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከማክሰኞ ጀምሮ ወደ ጦር ግንባር እንደሚዘምቱ ሰኞ ማምሻውን አሳውቀዋል። 


ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ "ኢትዮጵያ አሁን እያደረገችው ያለው ትግል የሁሉም ኢትዮጵያዊ ትግል ነው" ብለዋል። 


አክለውም "ትግሉ ልጆቻችን ሀገር እንዲኖራቸው የሚደረግ ትግል ነው። ልጆቻችን ክብርና ነጻነትን ለብሰው፣ በዓለም አደባባይ በኩራት ቀና ብለው እንዲሄዱ የሚደረግ ትግል ነው፤ በዓለም ላይ በክብር የምንጠራበት ስም እንዲኖረን የሚደረግ ትግል ነው። 


መኖር ወይም አለመኖራችንን የሚወስን ትግል ነው። ያለ ጥርጥር ግን እናሸንፋለን።" ሲሉ ፅፈዋል።

  

"ኢትዮጵያን ጠርቶ መሸነፍ ፈጽሞ የማይታሰብ ነው" ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ "ጊዜው ሀገርን በመሥዋዕትነት መምራት የሚያስፈልግበት ጊዜ ነው፤ ከእንግዲህ እኔ መከላከያን በግንባር ሆኜ ለመምራት ከነገ ጅምሮ ወደ ትግሉ ሜዳ እዘምታለሁ።" ብለዋል። 


ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ታሪክ ከሚያደንቃቸው የኢትዮጵያ ልጆች አንዱ ለመሆን የምታስቡ ሁሉ ለሀገራችሁ ስትሉ ዛሬውኑ ተነሡ፤ ግንባር ላይ እንገናኝ" በማለት ጥሪ አቅርበዋል። 


"የእኛ መዝመት የሚፈጥረውን ክፍተት ከግንባር የቀሩት በሙሉ ዐቅማቸው ሸፍነው ይሠራሉ፤ በግንባር ያልተሰለፉ የክልልና የፌደራል አመራሮች ከመቼውም ጊዜ በላይ የልማትና አስተዳደር ሥራዎችን በሙሉ ዐቅማቸው ይከውናሉ" ብለዋል። 


"ጎልማሶች በዘዴና በብልሃት አካባቢያቸውን እየጠበቁ፣ አረጋውያን እናትና አባቶች በጸሎት እየተጉ፣ ሁሉም ሰው ተባብሮ የኢትዮጵያን አሸናፊነት ያረጋግጣል" ሲሉም ነው በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ ባስተላለፉት መልእክት ያስነበቡት። 


"ለኢትዮጵያ ከእኛ በላይ ከየትም አይመጣም።" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ። "ከዚህ በኋላ በሩቁ ተቀምጠን ተቺና አራሚ የምንሆንበት ጊዜ አይደለም። መደረግ ያለበትን እኛው ራሳችን እናድርገው።" ብለዋል።



በተመሳሳይ የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባልና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አመራሩ አቶ ክርስቲያን ታደለም 


ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር አብረው እንደሚዘምቱ አሳውቀዋል።

"ለአገር አንድነትና ለሕዝብ ደኅንነት የምንሰስተው ሕይወት የለምና እኛም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር እንዘምታለን። ሕዝቤ ሆይ ተከተል " በማለት አቶ ክርስቲያን ታደለ ጥሪ አቅርበዋል።



አስተያየት ይለጥፉ

0 አስተያየቶች