For daily News Visite Agelgl Media
በኦሮሚያ ክልል ሆሮጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ አገምሳ ከተማ ትናንት(ማክሰኞ ነሐሴ 24 ቀን 2015 ዓ.ም) ከማለዳ ጀምሮ ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ ቢያንስ 55 ሰዎች መገደላቸው ተሰማ፡፡
የአከባቢው ነዋሪዎች እንደተናገሩት ለአንድ ዓመት ያህል የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች በመደበኛነት ተመድበው የአከባቢውን ፀጥታ ሲያስከብሩ ነበር፡፡
ይሁንና ባለፈው ዕሁድ ነሃሴ 22 ቀን 2014 የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ከከተማዋ መነሳታቸውን ተከትሎ የተለያዩ ስያሜ ያላቸው ታጣቂዎች በከተማዋ መፈራረቃቸውን የአይን እማኞች ገልፀዋል፡፡
አቶ ንጉሴ ባንጃ የተባሉ የአይን እማኝ «መንግስት ‘ሸኔ’ ያላቸው “የኦሮሞ ነጻነት ጦር” ሰኞ ጠዋቱን ገብተው ከተማዋን ተቆጣጥረዋታል፡፡” ብለዋል፡፡
የአይን እማኙ እንዳብራሩት ታጣቂዎቹ ከተማዋ ውስጥ ሙሉ በሙሉ መንቀሳቀስ ከጀመሩ በኋላ ወደ 59 መሳሪያ ከማህበረሰቡ አስፈትተው በዚያው ሰኞ ቀን ከተማዋን ለቀው ወጥተዋል፡፡
“ትናንት ማክሰኞ ጠዋት ደግሞ ፋኖ ነን ያሉ የታጠቁ አካላት ወደ ከተማዋ ገብተው ከኦነግ ጋር አብራችኋል በሚል በመደዳው ከተማዋ ላይ ተኩስ በመክፈታቸው ከ15 ሺህ የማያንሱ የከተማዋ ነዋሪዎች ከተማዋን ለቅቀው ለመሰደድ ተገደዋል” ነው ያሉት፡፡
ከትናንት ማታ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የ55 ሲቪል ዜጎች አስከሬን መቅበራቸውን የሚናገሩት የዐይን እማኙ “ከማህበረሰቡ 87 ሰዎች የጠፉ በመሆኑ የ32 ሰዎች አስከሬን በየጫካውና በየገደሉ እየፈለግን ነው” ሲሉም የችግሩን ስፋት አስረድተዋል፡፡
በመምህርነት ሙያ የተሰማሩት ቢቂላ ዓለሙ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ በበኩላቸዉ በጸጥታ ችግር ምክንያት ከየገጠር ቀበሌዎች የተፈናቀሉ የማህበረሰብ አካላት በዚሁ “የፋኖ ታጣቂዎች” ባሏቸው በተፈጸመው ጥቃት ከተማዋን ለቀው ተሰድደዋል፡፡
ኒሞና ዴሬሳ የተባሉ ሌላኛው በመምህርነት ሙያ የሚተዳደሩ ነዋሪ በበኩላቸው 20 አስከሬኖችን በዐይናቸው እንዳዩና የሟቾቹን ስም እንደመዘገቡም አስረድተዋል፡፡
እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ እማኝነት ከ40 በላይ ቁስለኞች መታከሚያ ቦታ እንኳ አጥተው ‘አስከፊ’ ያሉት ችግር ውስጥ ይገኛሉ፡፡
የነዋሪዎች ንብረት የሆኑ ከብቶችን ጨምሮ በርካታ ሃብት መዘረፋቸውንም አንስተዋል፡፡
በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የአሙሩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፋንታሁን ታዬ ስለሁኔታው ማብራሪያቸውን እንዲሰጡ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሳይሰጡ ቀርተዋል።
ስለ ጉዳዩ ምላሽ ለማግኘት ለኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ለኦሮሚያ ፀጥታና አስተዳደር ቢሮ እንዲሁም ለኦሮሚያ ኮሚዩኒኬሽን ባለስልጣናት የእጅ ስልካቸው ላይ ቢደውልም ምላሽ እንዳልሰጡ ዶይቼ ቬለ ዘግቧል።
0 አስተያየቶች