የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት(ተመድ) ለወራት ሲያካሂደው የነበረውን ወደ ትግራይ ክልል የሚያደርሰውን የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ማቋረጡን አስታወቀ።
የመንግሥታቱ ድርጅት እጅግ አስፈላጊ ነው ያለውን የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ወደ ትግራይ ማጓጓዝ ያቆመው የሰሜን ኢትዮጽያ ጦርነት ዳግም ማገርሸቱን ተከትሎ መሆኑን አስታውቋል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት (ኦቻ) እንዳለው፣ ካለፈው ሳምንት አጋማሽ ነሐሴ 18/2014 ዓ.ም. ጀምሮ በየብስ ወደ ትግራይ ይገባ የነበረው ሰብዓዊ እርዳታ ተቋርጧል።
እንዲሁም ከነሐሴ 19 ጀምሮ ደግሞ ወደ ትግራይ የሚደረጉ አስፈላጊ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት የአውሮፕላን በረራዎች ተቋርጠዋል ብሏል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ሰብዓዊ ቀውስ አሳሳቢ ሆኖ ቀጥሏል ያለው ኦቻ፤ ጦርነት እየተካሄደባቸው ባሉ አማራ እና አፋር ክልሎች ሰዎች ስለመፈናቀላቸው ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች እየወጡ ነው ብሏል።
በሰሜን ኢትዮጵያ የእርስ በእስር ጦርነት ተፋላሚ የሆኑት ወገኖች ለሰብዓዊነት ሲባል የተኩስ አቁም አድርገው ከቆዩ ከአምስት ወራት ገደማ በኋላ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ነሐሴ 18/2014 ዓ.ም. ዳግም ወደ ግጭት መግባታቸው ይታወሳል።
ለጦርነቱ ዳግም መቀስቀስ የትግራይ ኃይሎች የፌደራሉን መንግሥት ተጠያቂ ሲያደርጉ፤ መንግሥት ደግሞ ህወሓት የቀረበለትን የሰላም አማራጭ ወደጎን በመተው ዳግም ጥቃት ከፍቷል ይላል።
ግጭቱ ዳግም ማገርሸቱ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዜጎች ይቀርብ የነበረን የሰብዓዊ እርዳታ ማስተጓጎሉን የተባበሩት መንግሥታት ገልጿል።
ድርጅቱ በዕለታዊ መግለጫው መንግሥታዊ ካልሆኑ አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን የደኅንነት ሁኔታው ሲፈቅድ የሰብዓዊ እርዳታ ማድረስ እንደሚቀጥል የገለጸ ሲሆን፤ ቀድሞ ትግራይ ክልል የገባ ሰብዓዊ እርዳታ ግን እየተከፋፈለ መሆኑን ጠቁሟል።
የመንግሥታቱ ድርጅት በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ እርዳታ ሕግ መሠረት ተዋጊ ኃይሎች ሰብዓዊ እርዳታዎች እና የሰብዓዊ እርዳታ ሠራተኞች ያለ አንዳች ክልከላ በመላው ሰሜን ኢትዮጵያ እንዲንቀሳቀሱ በአስቸኳይ መፍቀድ አለባቸው ሲል ጠይቋል።
እንደ ተመድ ከሆነ ካለፈው ሳምንት አጋማሽ ጀምሮ ግጭት በመቀስቀሱ በየብስም ሆነ በአውሮፕላን ወደ ትግራይ እየገባ ያለ ጥሬ ገንዘብ፣ ሰብዓዊ እርዳታ እና የእርዳታ ሠራተኛ የለም።
የሰሜን ኢትዮጵያ የእርስ በእስር ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ በአማራ፣ በአፋር እና በትግራይ ክልሎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች አሉ።
ጦርነቱ ለሦስተኛ ዙር ዳግም ማገርሸቱ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል።
ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ላይ ጦርነቱ ማገርሸቱ ከተሰማ በኋላ የትግራይ ኃይሎች ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ቅጥር ግቢ ከግማሽ ሚሊዮን ሊትር በላይ ነዳጅ በኃይል መውሰዳቸውን ድርጅቱ ማስታወቁ ይታወሳል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ይህን የትግራይ ኃይሎች ተግባር “ዝርፊያ” ያለው ሲሆን፤ የፌደራሉ መንግሥት ደግሞ “ዝርፊያው የጦር ወንጀል ነው” ካለ በኋላ፣ የትግራይ ኃይሎች ነዳጁን መውሰድ ያስፈለጋቸው በቆቦና በአካባቢው ላይ ለተከፈተው ጥቃት ማስፈጸሚያ ለማዋል ነው ብሏል።
የትግራይ ኃይሎች በበኩላቸው ለድርጅቱ ያበደርነውን ነዳጅ መልሰን ወሰድን እንጂ ዝርፊያ አልፈጸምንም ሲሉ የዓለም ምግብ ፕሮግራምን አጥብቀው መተቸታቸው ይታወሳል።
የህወሓት ኃይሎች ነዳጁን በኃይል መውሰዳቸውን ተከትሎ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ነሐሴ 19/2014 ዓ.ም. ከሰዓት ላይ ባወጣው መግለጫ ያለ ነዳጅ እንደ ምግብ፣ ማደበሪያ፣ መድኃኒት እና ሌሎች መሠረታዊ ቁሳቁሶችን በትግራይ ማከፋፈል አይቻለኝም ብሏል።
ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት በትግራይ የምግብ እርዳታ ጠባቂ የሆኑ 5.2 ሚሊዮን ሕዝብ መኖሩን አስታውሶ ነበር።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም የሰብዓዊ እርዳታ በትግራይ ማድረስ የማይቻል ከሆነ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለከፋ የረሃብ አደጋ እንደሚያጋልጥ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ጠቅሷል።
ምንጭ:- ቢቢሲ
0 አስተያየቶች