Ticker

6/recent/ticker-posts

ህወሓት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ቀጥተኛ ያልሆነ ንግግር እያደረገ መሆኑን ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል መናገራቸውን ቢቢሲ ዘገበ

 

ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር)

ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (/


ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (/) ይህ የተደረገ ያለው ቀጥተኛ ያልሆነ ንግግር የተወሰነ ውጤት እያሳየ መሆኑንም ጨምረው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

 

ደብረጽዮን (/) ከቢቢሲ ኒውስ አወር ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ እንደተናገሩት በአፍሪካ ሕብረት፣ በተባበሩት መንግሥታት እና በኬንያ አማካኝነት በተዘዋዋሪ ዲፕሎማሲያዊ ንግግር እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

 

እየተካሄደ ነው ስለተባለው ቀጥተኛ ያልሆነ ውይይትን በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል አስካሁን የተባለ ነገር የለም።

 

በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውና ከአንድ ዓመት በላይ በዘለቀው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸውና ሚሊዮኖች ደግሞ ለመፈናቀል መዳረጋቸው ተዘግቧል።

 

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከቀናት በፊት ባወጣው ሪፖርት እንዳመለከተው በትግራይ ክልል ውስጥ 40 በመቶ የሚጠጉ ሰዎች በአስከፊ የምግብ እጥረት እየተሰቃዩ መሆናቸውን ገልጿል።

 

የህወሓት ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል እንደተናገሩት ጦርነቱን ለማስቆም ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እየተደረገ ያለው ቀጥተኛ ያልሆነ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ውጤት እያሳየ መሆኑንና የመሻሻል ምልክቶች እንዳሉ አመልክተዋል።

 

ደብረጽዮን ጨምረው ለቢቢሲ እንደተናገሩት እየተካሄደ ላለው ጦርነት ሰላማዊ መፍትሔ እንዲገኝ እንደሚፈልጉ ነገር ግን የትግራይ ሕዝብን መብት ለማስጠበቅ አስፋላጊ ሆኖ ከተገኘ እንደሚዋጉ ገልጸዋል።

 

ከቀናት በፊት አሶሺየትድ ፕሬስ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ለሰዓታት የዘለቀ ውይይት አድርገዋል የተባሉትን የአሜሪካውያን - ኢትዮጵያውያን የሕዝብ ጉዳዮች ኮሚቴ (አሜሪካን ኢትዮጵያን ፐብሊክ አፌይርስ ኮሚቲ) ሊቀመንበር የሆኑት አቶ መስፍን ተገኑን ጠቅሶ እንደዘገበው ጠቅላይ ሚንስትሩ መንግሥት ከትግራይ ኃይሎች ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑን አመልክቷል።

 

በውይይቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ "ድርድር ይኖራል። የአገሪቱን ጥቅም የሚያስቀድም ምክንያታዊ ድርድር ይኖራል" ስለማለታቸው ኤፒ ሊቀመንበሩን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

 

ይህንን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናገሩ የተባለውን ዘገባ ተከትሎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ህወሓት በሽብርተኝነት የተፈረጀ ድርጅት መሆን በመጥቀስ ድርድር እንደማይኖር ተናግረዋው ነበር።

 

ደብረጽዮን (/) ከቢቢሲ ኒወስ አወር ጋር ብዙም ባልተለመደ ሁኔታ በነበራቸው ቃለ ምልልስ ላይ 15 ወራት ከፈጀው ከዚህ ጦርነት ምን አተረፋችሁ ተብለው ለቀረበላቸው ጥያቄ "በዋናነት በፌደራል መንግሥቱ፣ በኤርትራ እና በአማራ ኃይሎች በትግራይ ሕዝብ ላይ ከታወጀው 'የዘር ማጥፋት' ዘመቻ ተርፈናል" ብለዋል።

 

ሊቀመንበሩ ከአንድ ዓመት በላይ በተደረገው ጦርነት ትግራይ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ጥፋት እና ውድመት መድረሱን አመልክተው "ዋናው ነገር በሕይወት መትረፋችን ነው፤ ወደ ፍጻሜው ለመጓዝ ዝግጁ ነን" ሲሉም አክለዋል።

 

ጦርነቱ ሲጀመር ፖለቲካዊ ዓላማ እንደነበራቸው በማስታወስም በሕይወት መትረፍ ብቻ በቂ ነው ተብለው የተጠየቁት ደብረፂዮን፣"ዋናው ነገር እንደ ሕዝብ እና እንደ መንግሥት ተርፈን መቀጠላችን ነው" ካሉ በኋላ "መሠረታዊ መብታችንን ማስከበር፣ ለደረሱ ውድመቶች እና ጥፋቶች ተጠያቂነት እንዲኖር ማድረግ እና ያሉንን ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ማድረግ ነው። ወደዚያም እያመራን ነው" ብለዋል።

 

ለደረሱ ውድመቶች እና የሰብዓዊ መብት ጥፋቶች ተጠያቂነት መኖር አለበት ያሉት ደብረጽዮን (/) በአሁኑ ወቅት በአፋር ክልል የህወሓት አማፂያን ውስን ተልዕኮ ብቻ ይዘው መግባታቸውን ተናግረዋል።

 

ጨምረውም የአፍሪካ ሕብረት፣ ኬንያ እና የተባበሩት መንግሥታት ጦርነቱን በማቆም ሰላማዊ መፍትሔ እንዲገኝ ለማስቻል እየሰሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።

 

ከዚሁ ጋር ተያይዞም ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ንግግር እና ውይይት መጀመሩን የተናገሩት ደብረጽዮን በዚህም የተነሳ ለውጦች እየታዩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

እየተደረገ ያለው ውይይት ጦርነት እንዲቆም፣ እርዳታና መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲቀርቡ፣ በድርድር ላይ የተመሰረተ ተኩስ አቁም እንዲኖር፣ የአማራና የኤርትራ ኃይሎች ከትግራይ እንዲወጡ እና ብሔራዊ ውይይት እንዲደረግ እንደሚፈልጉም ደብረጽዮን ተናግረዋል።

 

 ምንጭ፡ ቢቢሲ

አስተያየት ይለጥፉ

0 አስተያየቶች