Ticker

6/recent/ticker-posts

ግብፅ ጥገኝነት ጠያቂ ኤርትራውያንን በኃይል ወደ አገራቸው መመለሷን እንድታቆም ተጠየቀ

 

ኤርትራዊው ስደተኛ በግብፃውያን ሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ገንዘብ እንዲከፍል ስቃይ ተፈጽሞብኛል ይላል

ኤርትራዊው ስደተኛ በግብፃውያን ሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ገንዘብ እንዲከፍል ስቃይ ተፈጽሞብኛል ይላል

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሂዩማን ራይትስ ዋች የግብፅ ባለሥልጣናት ጥገኝነት ጠያቂ ኤርትራውያንን በኃይል ወደ አገራቸው ከመመለስ እንዲቆጠቡ ጠይቋል።

 

የመብት ድርጅቱ ጥር 19/2014 . ባወጣው ሪፖርት እንደሚለው የግብፅ ባለሥልጣናት ሕጻናትን ጨምሮ ጥገኝነት ጠያቂ ኤርትራውያንን ወደ ትውልድ አገራቸው ያለፍቃዳቸው እንዲመለሱ እያደረጉ ነው።

 

ታኅሣሥ 15/2014 .. ግብፅ 24 ጥገኝነት ጠያቂ ኤርትራውያንን ወደ አሥመራ መልሳለች። ከዚያ ቀደም ባሉት ጥቂት ወራት ደግሞ ሌሎች 15 ኤርትራውያንን መልሰው ነበር ተብሏል።

 

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ በኃይል ወደ ኤርትራ እንዲመለሱ የተደረጉ ሰዎች ስቃይ እና እጅግ አስከፊ የሆነ አያያዝ ያጋጠማቸው ሲሆን ያሉበት አድራሻም ያልታወቀ ሰዎች አሉ ብሏል።

 

"ግብፅ ወደ አገራቸው ሲመለሱ እስር እና ስቃይ የሚጠብቃቸውን ኤርትራውያንን በኃይል ከመመለስ ተቆጥባ የጥገኝነት ጠያቂ መብታቸውን ልትፈቅድ ይገባል" ሲሉ የሂዩማን ራይትስ ዋች የመካከለኛው ምሥራቅ እና የሰሜን አፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ስቶርክ አሳስበዋል።

 

እንደ ተባበሩት መንግሥታት የሰደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን አሃዝ ከሆነ በግብፅ ውስጥ የተመዘገቡ 20 ሺህ 778 ኤርትራውያን ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን አሉ።

 

ከእነዚህ ውጪ በግብፅ ያልተመዘገቡ ኤርትራውያን ስደተኞች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ አይታወቅም።

 

ሂዩማን ራይትስ ዋች እንደሚለው ታኅሣሥ 15 ላይ ወደ ኤርትራ በኃይል እንዲመለሱ የተደረጉት ኤርትራውያን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ያልተመዘገቡ ነበሩ።

 

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ግብፅ ጥገኝነት ጠያቂዎችን እስር፣ ስቃይ እና ለሕይወት አስጊ ወደሚሆንበት የትውልድ አገራቸው በኃይል መመለሷ ዓለም አቀፍ ሕግጋትን የሚጻረር ነው ብሏል።

 

ሂዩማን ራይትስ ዋች የግብፅ ባለሥልጣናት ስደተኞችን በኃይል ወደ ኤርትራ ከመላካቸው በላይ፤ የሰደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን አገልግሎትን እንዳያገኙ እየከለከለ ነው ሲልም ይከሳል።

 

ኤርትራውያኑ ስደተኞች በግብፅ እስር ቤቶች በተጨናነቀ ሁኔታ በቂ ምግብ እና የሕክምና አገልግሎት ተነፍገው ይገኛሉ ብሏል ሂዩማን ራይትስ ዋች።

 

ታኅሣሥ አጋማሽ ላይ ወደ ኤርትራ እንዲመለሱ ከተደረጉት ኤርትራውያን መካከል ዘጠኙ ታስረው ከነበሩበት በግብፅ ፖሊስ ካይሮ ወደሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲ የተወሰዱ ሲሆን፤ በኤምባሲውም ወደ ኤርትራ ለመመለስ የፍቃደኝነት ቅጽ ላይ ተገደው እንዲፈርሙ መደረጋቸውን ሂዩማን ራይትስ ዋች በሪፖርቱ አመልክቷል።

 

የመብት ተሟጋቹ ምንጮቼ ነገሩኝ እንደሚለው፤ ኤርትራውያኑ በማይገባቸው አርብኛ ቋንቋ የተጻፈ ስምምነት ላይ ፊርማቸውን እንዲያኖሩ ተገደዋል።

 

የኤርትራ መንግሥት በሂዩማን ራይትስ ዋች ባወጣው በዚህ ሪፖርት ላይ አስካሁን የሰጠው ምላሽ የለም።


ምንጭ፡ ቢቢሲ

አስተያየት ይለጥፉ

0 አስተያየቶች