Ticker

6/recent/ticker-posts

"አጀንዳው እየተፈበረከ ያለው አማራ ክልል ውስጥ ነው" የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት



ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሕወሓት ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ጋር በስልክ ውይይት አደረጉ ተብሎ የተሰራጨው መረጃ "ውሸት ነው" ሲሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሠ ቱሉ(ዶ/ር) ነግረውኛል ሲል ዶይቼ ቬለ ዘግቧል።



"ሰላማዊ ሁኔታ እንዳይፈጠር የሚፈልጉ" ያሏቸው ኃይሎች በተለይ አማራ ክልል አካባቢ "ሰላምና መረጋጋት እንዳይፈጠር እና የአማራውን ማህበረሰብ ለማነሳሳት የተፈጠረ አጀንዳ እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከየትኛውም የሕወሓት 'ታጣቂዎች' ጋር ንግግር አላደረጉም" ብለዋል። 



ዶይቼ ቬለ እንደዘገበው ሚኒስትሩ "ሁከት ለመፍጠር በሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ሕዝቡ መሪዎች ላይ አመኔታ እንዲያጣ ለማድረግ የተሠራ ነው" ሲሉ መረጃው ከእውነት የራቀ መሆኑን አስረድተዋል። 


"አጀንዳው እየተፈበረከ ያለው አማራ ክልል ውስጥ ነው" ብለዋል ሚኒስትሩ። 


"መንግሥት በድንበር አካባቢ ያለውን ሕብረረተሰብ በተለያየ መልኩ ሰላምና መረጋጋቱ እንዲመጣ እያገዘ አይደለም ፣ የፌዴራሉ መንግሥት በክልሉ ሰላም እንዲመጣ እየፈለገ አይደለም በሚል ለመቀስቀስና ለማነሳሳት የሚጠቀሙበት ነው።" በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።


ከቅርብ ቀናት ወዲህ ከትግራይ ክልል እየተፈናቀሉ ወደ አማራ ክልል እየገቡ ስላሉ ሰዎች ተጠይቀው ሲመልሱም "ሕወሓት ሕዝቡን እያስገደደ ወደ ጦርነት የሚማግድ በመሆኑ እና እርዳታ የሚተላለፍባቸውን መስመሮች በመዝጋቱ፣ አፈናውም እያንገበገበው ስለሆነ ነው።" ነው ብለዋል። 



በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወካይ የሌለውና አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ( ሕወሓት ) ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ በትዊተር ገፃቸው ላይ "ባለፉት 18 ወራት ውስጥ በድርጅቱ ሊቀመንበር ዶክተር በደብረፂዮን ገብረ ሚካኤል እና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ መካከል ምንም አይነት የስልክ ውይይት አልነበረም። ተመሳሳይ ጨዋታዎች በአዲስ አበባ በጣም የተለመዱ ናቸው።" በማለት መረጃው ሀሰት ስለመሆኑ ጽፈዋል።


አስተያየት ይለጥፉ

0 አስተያየቶች