ከህወሓት ከፍተኛ ባለሥልጣናት አንዱ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ እና የቀድሞው የኢትዮጵያ ጦር ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ጻድቃን ገብረተንሳይ የትግራይ ክልል መንግሥትን ወክለው እንዲደራደሩ መሾማቸውን ተገልጿል።
የክልሉ መንግሥት ይንህ ያለው ዛሬ መስከረም 1 ቀን 2015 ባወጣው መግለጫ ነው።
የክልሉ መንግሥት በመግለጫው ከኢትዮጵያ የፌድራል መንግሥት ጋር ለሚደረግ ድርድር "ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በፍጥነት እና በጋራ ስምምነት ግጭቶችን ለማቆም" ዝግጁ እንደሆነ ገልጿል።
"በአፍሪካ ህብረት የሚመራ ተዓማኒ የሰላም ሒደት እንጠብቃለን" ያለው የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ሊሳተፉ ይገባል ያላቸውን አካላት እና የሚኖራቸውን ሚና በመግለጫው ዘርዝሮ አቅርቧል።
"በጋራ ተቀባይነት ያላቸው አደራዳሪዎች እንዲሁም መተማመንን ለመገንባት የሚረዱ፣ ለሰላም ሒደቱ እምነት የሚፈጥሩ እና የስምምነቶችን ተግባራዊነት የሚከታተሉ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች" ሊሳተፉ እንደሚገባ የክልሉ መንግሥት ቅድመ ሁኔታ አስቀምጧል።
ከዚህ በተጨማሪ "ለሰላም ሂደቱ ተዓማኒነት አስፈላጊ እገዛ እና ምክር የሚያቀርቡ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች" ሊሳተፉ እንደሚገባ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት በመግለጫው ጠቁሟል።
ምንጭ:- ዶቼ ቨሌ
0 አስተያየቶች