የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት የደሴ እና የኮምቦልቻ ከተሞችን ጨምሮ ሌሎች አካባቢዎችን ከህወሓት ኃይሎች አስለቅቆ መቆጣጠሩ ተገለጸ።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሰኞ ኅዳር 27/2014 ዓ.ም
አመሻሽ ላይ እንዳስታወቀው የደቡብ ወሎ ዞን ዋና ከተማ የሆነችው የደሴ ከተማ እንዲሁም የንግድና ኢንዱስትሪ ከተማ የሆነችው የኮምቦልቻ ከተማ ከአማጺያኑ ነጻ መውጣታቸውን ገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና የክልል የፀጥታ ኃይሎች በጥምረት ባካሄዱት ዘመቻ በምሥራቅ ግንባር ባቲን፣ ቀርሳን፣ ገርባንና ደጋንን እንዲሁም በሐርቡ ግንባር የቃሉ ወረዳን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠራቸውን መንግሥት አሳውቋል።
ከአንድ ወር በላይ በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር የቆዩት የደሴ እና የኮምቦልቻ ከተሞች በኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት፣ በአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻዎች አማካይነት ነጻ መውጣታቸው ተገልጿል።
በአማራ ክልል የደቡብ ወሎ ዞን ዋና ከተማ የሆነችው ደሴ ከተማን የህወሓት ኃይሎች የተቆጣጠሯት ጥቅምት
20/2014 ዓ.ም ሲሆን፤ በማስከተልም በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኘው የኮምቦልቻ ከተማም በሕወሓት ኃይሎች መያዟ ይታወሳል።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ ትግራይ ውስጥ የተጀመረው ጦርነት ወደ አማራና አፋር ክልሎች ከተስፋፋ በኋላ ከባድ ጦርነት ሲካሄድ ቆይቶ የትግራይ ኃይሎች በሁለቱ ክልሎች ውስጥ የተለያዩ ቦታዎችን ለመቆጣጠር ችለው ነበር።
ከአንድ ወር በላይ በበትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ስር የቆየችው የደሴ ከተማ ከአዲስ አበባ 385 ኪሎ ሜትር የምትርቅ ሲሆን በአማራ ክልል ውስጥ ካሉ ትልልቅ ከተሞች መካከል አንዷና የደቡብ ወሎ ዞን ዋና ከተማ ናት።
በዚህ ዓመት በአማራና በአፋር ክልሎች ውስጥ ከጥቅምት ወር መጀመሪያ አንስቶ የተባባሰው ጦርነት ከሰሜን ወሎ ወደ ደቡብ ወሎ በመስፋፋት ወሳኝ የሚባሉት የደሴና የኮምቦልቻ ከተሞች በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር ከገቡ በኋላ ወደ ሰሜን ሸዋ ተስፋፍቶ ቆይቷል።
ከሁለት ሳምንት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ጦር ግንባር በመሄድ ሠራዊቱን መምራት መጀመራቸውን ተከትሎ የህወሓት ኃይሎች ግስጋሴ ከመገታቱ በተጨማሪ ይዘዋቸው ከነበሩ የአፋርና የአማራ ክልል አካባቢዎች ለቀው ለመውጣት ተገደዋል።
በህወሓት መሪዎች በኩል ግን ኃይሎቻቸው እንዲወጡ የተደረገው "በስልታዊ ውሳኔ" መሆኑ የተገለጸ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንን የሆኑት ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ "አማጺው ሽንፈት ገጥሞት" እንዲወጣ መደረጉን ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ ትግራይ ውስጥ የተቀሰቀሰው ጦርነት ባለፈው ሰኔ ወር ወደ አፋርና አማራ ክልሎች ተስፋፍቶ እስካሁን እየተካሄደ ይገኛል።
የህወሓት ኃይሎች ወደ አማራና አፋር ክልል በመግባት ዘመቻ በማካሄዳቸው በሁለቱ ክልሎች ውስጥ የተለያዩ ቦታዎችን ይዘው ወደ አዲስ አበባ ለማቅናት ፍላጎት እንዳለቸው ሲገልጹ ቆይተው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ጦር ግንባር በመሄድ ሠራዊቱን ለመምራት መወሰናቸውን ተከትሎም በህወሓት ኃይሎች ተይዘው የነበሩ ቦታዎችን ለማስለቀቅ ውጊያዎች ተጠናክረው እየተካሄዱ ነው።
በዚህም ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ታሪካዊቷና በቅዱስነት የምትታወቀው የላሊበላ ከተማን ጨምሮ ቁልፍ ወታደራዊ ጠቀሜታ አላቸው የሚባሉት በአፋር ክልል ጭፍራ በአማራ ክልል ደግሞ የጋሸና ከተሞች በመንግሥት ኃይሎች ቁጥጥር ስር መግባታቸው ተዘግቧል።
ከዚህ በተጨማሪም በሰሜን ሸዋ፣ በደቡብ እና በሰሜን ወሎ ውስጥ በህወሓት ኃይሎች ተይዘው የነበሩ አካባቢዎችም በመንግሥት ቁጥጥር ስር መግባታቸው ተገልጿል።
0 አስተያየቶች