Ticker

6/recent/ticker-posts

- የአንድ እሁድ ገጠመኝ -


ከዓመታት በፊት የሆነ ገጠመኝ ነው። 2004 ዓ.ም ክረምት ላይ ይመስለኛል። አንዲቷ የቤት ልጅ ቀጥራኝ ላገኛት እየሄድኩ ነው። ለእኔ የቤት ልጅ መሰለችኝ እንጂ እሷ ቀላል ሰው አደለችም። እና ስንገናኝ ሜክሲኮ ካፌ አረፍ ብለን እንድንጫወት ሐሳብ አቀረብኩ። ልብ በሉ በኪሴ የያዝኩት 16 ብር ብቻ ነው፤ ከነ ትራንስፖርት መመለሻዬ። ገንዘቡ ሜክሲኮ ካፌ ውስጥ ሻይና ቡና ለመጠጣት ይበቃል።


ቀበጢት ግን "እዚያ አይሆንም" አለች። 


ልቤ እየደነገጠ "ታዲያ የት ይሁን?" ብዬ ብላት


"ዋቢ ሸበሌ እንሂድ" ብላ እርፍ.... ጉድ ፈላ!


"ኧረ ተይ ግዴለሽም እዚሁ ይሻለናል!" ብዬ ባንገራግርም በእጄ የምትል አልሆነችም። ምን አማራጭ አለኝ? 'እግዜር የዛሬን አውጣኝ' እያልኩ ተከተልኳት።


አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ተማሪ እያለሁ የሰማሁትን አንድ ታሪክ ማሰብ ጀመርኩ። በየወሩ ግማሽ የዲግሪ ደሞዝ እየተላከለት የሚማር አንድ ቀብራራ ተማሪ ነበር። ከኮፒና ከሻይ የተረፈውን ገንዘብ ቆንጆ ሴት ተማሪዎችን ለማማለል ይጠቀምበታል። ሁልጊዜ ፋሲካ የለምና ይሄ ጎረምሳ አንድ ቀን ጉድ ሆነ። ከባድ ሴት ላይ ጣለው። የቦሌ ልጅ ናት አሉ፤ ባገኛት ቁጥር "መቼ ነው ወጣ ብለን የምንዝናናው?" ይላታል።


እሷ ስቃ ታልፈዋለች።


በሌላ ጊዜም "ቅዳሜ ብጋብዝሽስ?" ይላል። አስከትሎም ክለብ ሲጨፍሩ የማደር ሐሳብ ያመጣል።


ነገሩ ሲደጋገምባት አንድ ቀን "እሺ" አለችው። ቅዳሜ ምሽቱን ተቃጠሩ። ከስድስት ኪሎ ላዳ ይዘው ወደ ቦሌ ነጎዱ። ጎረምሳው በኪሱ 6 መቶ ብር ይዟል። በእሷ ምርጫ ወደ አንድ ሆቴል ገቡ። በእሷ ምርጫ እራት ተበላ። በእሷ ምርጫ መጠጦች ወረዱና ተጠጣ። ምሽቱ ገፍቷል። ሙዚቃው ኩልል እያለ ይንቆረቆራል፤ ልስልስ ያለ ሙዚቃ። ጎረምሳው ግን የክለብ አይነት የሚያስጨፍር ዘፈን ቢሆንለት ምኞቱ ነበር። ወደ ግቢ ሲመለስ "አስጨፈርኳት" ለማለት። በመጨረሻ ሂሳብ መጣ። ቀብረር ብሎ የሂሳብ ደብተሩን ገለጠው። ዐይኑን ማመን አልቻለም። 1234 ብር ይላል። የሆነ የድምር ሥህተት እንዳለው እርግጠኛ ነበር። ደጋግሞ አጤነው። ለውጥ የለም። ቆንጂት መደንገጡን ተመልክታ የሂሳብ ደብተሩን ተቀብላ አየችው። ምንም አልመሰላትም።


"ክፈልና እንውጣ!" አለች።


"የያዝኩት 6 መቶ ብር ነውኮ" አለ የሞት ሞቱን። ከሆቴሉ ጋርዶች የሚጠብቀውን ቡጢና ጡጫ ሲያስብ ላብ አጠመቀው።  


ቆንጂት ፈገግ ብላ የገንዘብ ቦርሳዋን ከፍታ 1300 አውጣችና የሂሳብ ደብተሩ ውስጥ እየሸጎጠች፣


"ሌላ ጊዜ ያላቅምህ አትንጠራራ" ብላው ውልቅ አለች።


ጎረምሳው ከቡጢና ጡጫ መትረፉን ሲያስብ ደስ አለው። ዳሩ ግን የመዋረዱን ስሜት ምን ያድርገው? ጥፍር ውስጥ ገብቶ ቢደበቅ ደስ ባለው። አቀርቅሮ ከሆቴሉ ወጣ።


ከዚያች ምሽት ወዲህ የግብዣ ነገር ሲነሳ ትውስ የሚለው የቦሌዋ ልጅ አሽሟጣጭ ሳቅ እና "1234 ብር" የሚል ሂሳብ ነው። 


ይሄን ታሪክ የሰማሁ እለት ለአንድ አፍታ መሳቄን አልክድም። ግን ደሞ በሆዴ 'ከእንደዚህ ያለ ውርደት ሰውረኝ' ስል ነበር። የወንድነት ስሜት ሴት ፊት መዋረድን ከሞት በላይ አግዝፎ የማሳየቱ ነገር ሳስበው ይደንቀኛል። (ጥንት በአያቶቻችን ዘመን ጦር ሜዳ ላይ ሴቶችን ከኋላ የሚያሰልፉት ያለ ምክንያት አይደለም፤ ወንዶች ሚስታቸውና ሌሎች ሴቶች ፊት ሆነው ወደ ኋላ መሸሽን ከሚያስቡ ይልቅ ዐይናቸው እያየ ሞታቸውን እንደሚመርጡ የተመሰከረ ጉዳይ ስለሆነ ነው።)


እናም የዚያን እለት ኪሴ ስላለው ገንዘብ ማነስ እያሰብኩ፣ ስለሚጠብቀኝ ውርደት እየተጨነቅኩ፣ እዚያ ሆቴል ውስጥ ምንም ነገር ሳንመገብና ሳንጠጣ ልንወጣ የምንችልበትን መንገድ እያውጠነጠንኩ፣ በደመነፍስ እከተላታለሁ። ደሞ እኮ በሆነ ነገር አስቀይሜአት ከሳምንት ኩርፊያ በኋላ ነው የተገናኘነው። ድሮም ካልተገናኘን ስትለኝ ሸክኮኝ ነበር። ምነው "እሺ" ያልኩበት ምላሴ በተቆረጡ...


እንዲህ በውስጤ እያሰብኩና እየተጨነቅኩ፣ አልፎ አልፎ  ሰማዩን በቆረጣ እያየሁ እየጸለይኩ፣ ሸበሌ ስንደርስ ምን ቢሆን ጥሩ ነው?


"እድሳት ላይ ነው" ብለው ዘበኞች መለሱን። እውነት እውነት እላችኋለሁ እንዴት እንደገረመኝ። ከጊዜያት ሁሉ መርጦ እኔን ከውርደት ሊያወጣ ጸሎቴ፣ ሸበሌን እድሳት ላይ ጣደው! አለፍ ብለን ኮሜርስ አጠገብ ቨርጂን ካፌ ሁለት ሻይና አንድ ተቆራጭ ኬክ በልተን ጠጥተን ወጣን፣ አሥራ ሁለት ብር ከፈልኩ።


መልካም ቀን 🙏


✍መሳፍንት ተፈራ 

አስተያየት ይለጥፉ

0 አስተያየቶች