ፓርቲው እያካሄደ ባለው 1ኛ ጠቅላላ ጉባኤ የፓርቲውን ፕሬዜዳንት እና ምክትል ፕሬዜዳንቶች ምርጫ አካሂዷል።
ጉባኤው ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር )ን በሲዳማ ክልል ፕሬዝዳንት ደስታ ሌዳሞ ጥቆማ የፓርቲው ፕሬዚዳንት አድርጎ መምረጡን ምንጮች ገልፀዋል።
ፓርቲው ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለት ምክትል ፕሬዝዳንቶች እንዲኖሩ በማድረግ አደም ፋራህን እንዲሁም ደመቀ መኮንን ምክትል ፕሬዚዳንቶች በማድረግ መርጧል።
አደም በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፕሬዝዳንት አሻድሊ ሀሰን ጥቆማ የቀረቡ ናቸው።
የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ጥቆማ እንደቀረቡ ታውቋል።
የምክትል ፕሬዝዳንቶች ጥቆማ በተሰጠበት ወቅት ተቃውሞ ተነስቶ እንደነበርም ምንጮች ጠቅሰዋል።
አንድ ስሙ ያልተገለፀ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል፤ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት አደም ፋራህ እጩ ሆነው እንዳይቀርቡ ተቃውሞ አቅርቦ እንደነበርም ታውቋል።
ተቃውሞ ያቀረቡት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ፥
" አቶ አደም እጩ ሆነው መቅረብ የለበትም ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም አደም በአፋር እና ሶማሌ አካባቢ በተለይ በኢሳ እና አፋር ግጭት ላይ በቀጥታ እጅ ያለው ሰው በመሆኑ ይህን ግዙፍ ፓርቲ ምክትል ሆኖ መምራት ስለማይችል በእራሴ በኩል እቃወማለሁ "ብለዋል።
ምንም እንኳን አደም ፋራህ ላይ ተቃውሞ ቢቀርብም በአንድ ሶስተኛ ድምፅ አሸናፊነት እጩ ሆነው ሊቀርቡ ችለዋል።
በዚህ ሂደት የጉባኤ ተሳታፊዎች ድጋፋቸውን ለመግለፅ ያልተቋረጠ ከፍተኛ ጭብጨባ ያሰሙ ሲሆን ዶ/ር ዐቢይ ፤ "ይሄ ትክክል አይደለም ...undemocratic አትሁኑ፤ የፈለገ ሰው ይመርጣል፤ የፈለገ ይቃወማል። በግርግር በወከባ፣ ምናምን የሚደረግ ነገር አይደለም። ጥሩ አይደለም እንደዚህ " ሲሉ ተደምጠዋል።
ከዚህም ለኃላ በተካሄደው ምርጫ አቶ አደም 1ሺህ 330 ድምፅ አግኘተው ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል።
0 አስተያየቶች