ምስራቅ ወለጋ ዉስጥ ከ200 በላይ ሰዎች ተገደሉ፣ 40 ሺሕ ያሕል ተፈናቀሉ
የጀርመን ድምፅ (DW) እንደዘገበው በኦሮሚያ መስተዳድር ምሥራቅ ወለጋ ዞን፣ ኪራሙ ወረዳ ዉስጥ «የኦነግ-ሸኔ ሸማቂዎች» ናቸዉ የተባሉ ታጣቂዎች በከፈቱት ጥቃት ከ200 በላይ ሰዎች መግደላቸዉን የአካባቢዉ ነዋሪዎች አስታውቀዋል።
በጥቃቱ ምክንያትም ከ40 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል።
ዶቼቨለ በስልክ አነጋገርኳቸው ያላቸው የዓይን ምስክሮች እንዳሉት ታጣቂዎቹ ካለፈዉ ሳምንት ሮብ ጀምሮ በወረዳዉ የሚገኙ 6 ቀበሌዎችን ወርረዉ የአማራ ተወላጅ የሆኑ ነዋሪዎችን ልጅ ካዋቂ፣ ሴት ከወንድ ሳይለዩ በጥይትና በገጀራ ገድለዋቸዋል።
ከጥቃቱ ያመለጡ አንድ ዓይን ምስክር እንዳሉት አማርኛ ተናጋሪ የሆኑ የአካባቢዉ ነዋሪዎች ከየቤታቸዉ እንዳይወጡ፣ ከወጡም ዉጪ እንዳያመሹ የሚያስጠነቅቅ ወረቀት ባለፈዉ ነሐሴ 11 ቀን 2013 ዓ.ም በየሥፍራዉ ተለጥፎ ነበር።
«ነዋሪዎቹ ለአንድ ሳምንት ያክል በየቤታቸው "ተሸሽገው" ከሰነበቱ በኋላ የአካባቢዉ ባለስልጣናት ማስጠንቀቂያዉን እየገነጠሉ ስለጣሉት ነዋሪዎችም ሠላም ነዉ ብለዉ ከየቤታቸዉ መዉጣት ጀመሩ፣ ከዚያም ታጣቂዎች አካባቢዉን ወረው ከየቤታቸው የወጡትን ገደሉ፤ ከብታቸዉን ዘረፉ፤ እቤት ዉስጥ ሰው "ተቀምጦ" የቤቱን ጣራ እየነቀሉ ወሰዱት።»ይላሉ።
የዓይን ምስክሩ እንዳሉት በአካባቢዉ ልዩ ኃይል ከገባ በኋላ ከትናንት በስቲያ ብቻ የአካባቢው ነዋሪዎች 72 ሰዎችን ቀብረዋል።
ሐሮ ከተባለ ቀበሌ የተፈናቀሉ ሌላ የዓይን ምስክር ለጣቢያው እንዳሉት ደግሞ ታጣቂዎቹ በተለያዩ ቀበሌዎች የገደሏቸዉ ሰዎች ቁጥር ከ200 ይበልጣል።
ከሟቾቹ ቢያንስ አራቱ የልዩ ኃይል አባላት መሆናቸው ዶቼቬሌ ጠቅሷል።
የዓይን ምስክሩ አክለዉ እንዳሉት ከ40 ሺህ የሚበልጥ ሕዝብ ተፈናቅሏል።
ስለጥቃቱና ስለደረሰዉ ጉዳት ለማረጋገጥ ስልክ ከደወልናላቸዉ የምሥራቅ ወለጋ ዞንና የኦሮሚያ ባለስልጣናት መካከል አንዱ ማንነታችንን ከጠየቁ በኋላ «ሥራ ላይ ነኝ» በማለት ስልኩን ዘግተዋል።
"ሌሎቹ በተደጋጋሚ ብንደዉልም ስልካቸዉን አያነሱም።" ሲል ጣቢያው ዘግቧል።
ምንም አስተያየቶች የሉም