የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በኢትዮጵያ እየተደረገ ባሉት የመብት ጥሰት እና ወታደራዊ ዘመቻ ሃገሪቱን ከአፍሪቃ የዕድገት እና ዕድል ድንጋጌ በእንግሊዝኛ ምሕጻሩ (AGAOA) ማገዳቸውን አስታወቁ።
ጆ ባይደን በኮንግረንሱ ቀርበው እንዳሉት ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት የሲቪል አስተዳደሮችን ያስወገዱት ጊኒ እና ማሊም ዕድሉ ታግዶባቸዋል።
AGAOA 2000 ከሰሃራ በታች የአፍሪቃ ሃገራት ከቀረጥ ነጻ ምርቶቻቸውን ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ማስገባት የሚያስችላቸው ዕድል ነበር።
ኢትዮጵያ በዚሁ ዕድል ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ቡናን ጨምሮ ጨርቃ ጨርቅ እና የቆዳ ውጤቶችን በመላክ የውጭ ምንዛሪ ታገኝበት ነበር።
በሌላ ዜና የሕወሓት ኃይሎች ወደ መዲናይቱ አዲስ አበባ የሚያደርጉትን ጉዞ አሜሪካ እንደምትቃወም በአፍሪቃ ቀንድ የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ መልዕክተኛ ጄፈሪ ፌልት ማን አስታውቀዋል።
ተፋላሚዎቹ ወደ መዲናይቱ የሚያደርጉት «የመስፋፋት ጉዞ ተቀባይነት የሌለው ነው »ብለዋል።
በኢትዮጵያ ያለው ወቅታዊ ሁኔታም ከወራት በፊት ከነበረው በእጅጉ አሳሳቢ ነው ሲሉ ጠቅሰዋል። ዉግያው በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ የሀገሪቱን አንድነት ለአደጋ የሚያጋልጥ ነው ብለዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ባለው የሰብአዊ ሁኔታም አሜሪካን እንዳስደነገጣት ፌልት ማን ገልጸዋል።
በግጭቱ ውስጥ ያሉ ሁሉም ወገኖች ተሰባስበው ለችግሩ መፍትሔ እንዲሹ እና የሰብአዊ ርዳታ እንዲደርስ አሳስበዋል።
ልዩ መልዕክተኛው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አብዛኛውን በመንግስት በተደረጉ ክልክለዎች ምክንያት ረሃብ አልያም ለረሃብ የቀረበ ምልክት መታየቱን ዩናይትድ ስቴትስ እንደተረዳች ገልጸዋል።
0 አስተያየቶች