የሚኒስትሮች ምክርቤት በመላ ኢትዮጵያ ተግባራዊ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ ዛሬ ማክሰኞ አውጇል፡፡
አዋጁ የታወጀው የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ‹‹ሁሉም ዜጋ ያለውን መሳሪያ ይዞ ይዝመት›› ካሉ ከሁለት ቀናት በኋላ ነው፡፡
በአስቸኳይ አዋጁ መሰረት ቤት ለቤትን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ፍተሻ ሊደረግ እንደሚችል፤ በየትኛውም የሃገሪቱ ክፍል መከላከያ ኃይልን ወይም የትኛውንም ሌላ የጸጥታ አካል በማሰማራት ሰላምና ፀጥታ እንዲያስክብሩ ትዕዛዝ ሊሰጥ እንደሚችል፣ እድሜያቸው ለወታደራዊ አገልግሎት የደረሱ እና የጦር መሳርያ የታጠቁ ዜጎች ወታደራዊ ስልጠና እንዲወስዱ፣ ወታደራዊ ግዳጅ እንዲቀበሉ፣ ወይም ይህን ማድረግ የማይችሉ ከሆነም በአማራጭ ትጥቃቸውን ለመንግስት እንዲያስረክቡ ሊያዝ ይችላል፣ የሰዓት ዕላፊ ገደብ ሊወሰን እና ማናቸውም የህዝብ የመገናኛ እና የህዝብ መጓጓዥ ዘዴ እንዲዘጋ ወይም እንዲቋረጥ ሊያዝ ይችላል፡፡
መንግስት ‹‹የሽብር ቡድኖች›› ሲል ከሚጠራቸው ከሕወሓትና ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ጋር ይተባበራል ተብሎ ‹ምክንያታዊ በሆነ መልኩ› የተጠረጠረ ማንኛውንም ሰው ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በቁጥጥር ሥር ለማድረግ፣ እንዲሁም አዋጁ ተፈፃሚ ሆኖ ባለበት ጊዜ ድረስ ይዞ ለማቆየት ወይም በመደበኛ ሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግ እንደሚችል ይደነግጋል፡፡
የትግራይ ተፋላሚ ኃይሎች ሰሞኑን ስትራቴጂያዊ ከተማ የሆነቺው ደሴንና የኢንዱስትሪ ማዕከሏ ኮምቦልቻን ተቆጣጠርን ሲሉ የኢትዮጵያ መንግስት ግን ሃሰት ነው ሲል አጣጥሎታል፡፡
የፌደራል መንግሥት ትናንት የሕወሓት ኃይሎች በኮምቦልቻ 100 ወጣቶችን እንደገደሉና በደሴም የቤት ለቤት ብርበራ ማድረጋቸውን ገልጿል፡፡
መንግሥት በወሎ ግንባር በነበረው ውጊያ ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ ኃይሎች ከሕወሓት ጋር መሳተፋቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገልፀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ይበሉ እንጂ ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ ኃይሎች ስላሏቸው ሰዎች ዜግነት ያሉት ነገር የለም፡፡
የትግራይ ተፋላሚ ኃይሎች ወደ ዓፋር ክልል ሚሌ እያቀኑ መሆናቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ይፋ
አድርገዋል፡፡
በትግራይ ክልል ባለፈው ዓመት የተጀመረው ደም አፋሳሽ ጦርነት አድማሱን አስፍቶ ወደ ዓፋርና አማራ ክልሎች ከገባ ወራት ተቆጥረዋል፡፡
በአጠቃላይ በሚልዮኖች
የሚቆጠሩ ሰዎች ለመፈናቀልና
ለረሃብ ሲዳረጉ በሺህዎች
የሚቆጠሩ ደግሞ ተገድለዋል፡፡
0 አስተያየቶች