Ticker

6/recent/ticker-posts

በሰሜን ኢትዮጵያ ሰብዓዊ እርዳታ የሚስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር 9.4 ሚሊዮን መድረሱን የተባበሩት መንግሥታት አስታወቀ

 

 

በሰሜን ኢትዮጵያ ባለው አውዳሚ ጦርነት ምክንያት አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር ወደ 9.4 ሚሊዮን መድረሱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።

 

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ቃል አቀባይ ቶመሰን ፊሪ፤ በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ወስጥ የሚገኙ 9.4 ሚሊዮን ሰዎች አስከፊ ሁኔታ ላይ ናቸው  ሲሉ  አርብ ዕለት በጄኔቭ  ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

 

ከእነዚህ መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት ማለትም 7.8 ሚሊዮን የሚሆኑት በጦርነቱ ምክንያት ሰብአዊ እርዳታ ማድረስ አዳጋች የሆኑባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ሰዎች ናቸው ብለዋል ቃል አቀባዩ።

 

የሰብዓዊ እርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ለውጥ የታየበት በአማራ ክልል መሆኑን የጠቀሱት ቃል አቀባዩ፤ በአሁኑ ጊዜ በዚህ ክልል ብቻ 3.7 ሚሊዮን ሰዎች የሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል።

 

ከትግራይ፣ ከአማራ እና ከአፋር የተሰበሰቡ መረጃዎች እንዳመለከቱት በሦስቱ ክልሎች ከሚገኙ ሕጻናት መካከል 16 እስከ 18 በመቶ የሚሆኑት የተመጣጠነ ምግብ እጥረት አጋጥሟቸዋል።

 

ከዚህ በተጨማሪም ነፍሰጡር ከሆኑ እና ከሚያጠቡት እናቶች መካከል 50 በመቶ ያህሉ በተመሳሳይ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንዳጋጠማቸው መለየቱ እና ይህም የመንግሥታቱን ድርጅተ በእጅጉ እንዳሰሰበ ቃል አቀባዩ ጨምረው አብራርተዋል።

 

የተባበሩት መመንግሥታት የምግብ አቅርቦት የጫኑ ተሸከርካሪዎች ከኮምቦልቻ ወደ ደቡባዊ ትግራይ እየላከ እንደሆነ ገልጾ፣ በቀጣይ ቀናት 2200 ሜትሪክ ቶን ሕይወት አደን ምግብ መቀለ ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተነግሯል።

 

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በትግራይ 2.5 ሚሊዮን ሕዝብ ጋር መድረስ ሲኖርብኝ እስካሁን መድረስ የቻልኩት 180 ሺህ የሚሆኑትን ብቻ ነው ይላል።

 

"ረሃብ በኢትዮጵያ አልታወጀም ግን . . . ያለውን አስከፊ ሁኔታ ሊገልጽ የሚችል ቃላት የሉንም" ያሉት ቃል አቀባዩ በኢትዮጵያ ያለው ሰብዓዊ ቀውስ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን አመልክተዋል።

 

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የዓለም ምግብ ፕሮግራም በደሴ እና ኮምቦልቻ 10ሺህ ሰዎች የምግብ እርዳታ ማቅረቡንም አስታውሰዋል።

 

ቃል አቀባዩ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ደሴ እና ኮምቦልቻ በትግራይ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የእርዳታ አቅርቦት ሥራ ማከናወኑን ተናግረዋል።

 

ቃል አቀባዩ ከአራት ቀናት በፊት በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር በሚገኘው ኮምቦልቻ ውስጥ ያሉት የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ማከማቻ መጋዘኖቹ መዘረፋቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።

 

ቶምሰን ፊሪ፤ የዓለም ምግብ ፕሮግራም በአማራ ክልል ኮምቦልቻ የሰብዓዊ እርዳቃ እንዲያቀርብ ፍቃድ ካገኘ በኋላ ድርጅቱ ባደረገው ቅድመ ግምገማ መሠረት በርካታ ንብረቶቹ መውደማቸውን እና መጋዘኖቹ ውስጥ የነበረ እህልም መዘረፉን አሳይቷል ብለው ነበር።

 

ቶመሰን ፈሪ ትናንት በሰጡት መግለጫ የዓለም ምግብ ፕሮግራም እስካሁን ድረስ በሰሜን ኢትዮጵያ 3.2 ሚሊዮን ሰዎች የምግብ እርዳታ ማቅረቡን ተናግረዋል።

 

ከእነዚህም መካከል 220 ሺህ የሚሆኑት በአማራ እንዲሁም 124 ሺህ የሚሆኑት ሰዎች ደግሞ በአፋር የሚገኙ ስለመሆናቸው ተመልክቷል።

 

በህወሓት ኃይሎችና በኢትዮጵያ መንግሥት ሠራዊት መካከል ትግራይ ውስጥ ተቀስቅሶ ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ጦርነት ወደ አማራና አፋር ክልሎች ተስፋፍቶ እየተካሄደ ይገኛል።

 

በጦርነቱ ሳቢያ በርካታ ሺዎች በጦርነቱ ምክንያት ሳይሞቱ እንዳልቀሩ ሲገመት፣ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በረሃብ አፋፍ ላይ መሆናቸውና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደግሞ ለመፈናቀልና ለችግር መዳረጋቸውን የተባበሩት መንግሥታት አመልክቷል።

 

ዘገባው የቢቢሲ ነው



አስተያየት ይለጥፉ

0 አስተያየቶች