Ticker

6/recent/ticker-posts

የአሃዱ ሬድዮ ጋዜጠኛ ልዋም አታኽልቲ ከ21 ቀናት እስር በኋላ በዋስትና ተፈታች

ልዋም አታኽልቲ


ለ21 ቀናት በእስር ላይ የቆየችው የአሃዱ ኤፍ ኤም ሬድዮ ጋዜጠኛ ሉዋም አታኽልቲ፤ 10 ሺህ ብር ዋስትና ትናንት አርብ ከእስር መፈታቷን ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘግቧል። 


የጣቢያው ዜና አርታኢ የሆነው ክብሮም ወርቁም፤ በ15 ሺህ ብር ዋስ እንዲፈታ በፍርድ ቤት መወሰኑን የጋዜጠኞቹ ጠበቃ አቶ ጥጋቡ ደሳለኝ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።  


የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ይግባኝ ሰሚ ችሎት፤ ጋዜጠኛ ሉዋም በዋስትና እንድትፈታ የወሰነው ከሶስት ቀን በፊት ማክሰኞ ጥቅምት 30፤ 2014 ነበር። ሆኖም “በአሰራር አለመናበብ ችግር ምክንያት” እስከ ዛሬ ስድስት ሰዓት ድረስ ሳትፈታ በእስር መቆየቷን ጠበቃዋ አቶ ጥጋቡ ገልጸዋል።  


የጋዜጠኛዋ ጉዳይ ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተወሰደው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ላይ ይግባኝ በመጠየቁ ነው። 


የሉዋምን የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ጉዳይ ሲመለከት የቆየው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት፤ ጋዜጠኛዋ በዋስትና እንድትለቀቅ ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ ነው ፖሊስ ይግባኝ የጠየቀው። 



ፍርድ ቤቱ ባለፈው ሳምንት አርብ በዋለው ችሎት የፖሊስ ምርመራ የደረሰበትን ደረጃ አድምጦ ነበር። በዕለቱ በነበረው ችሎት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ለብሔራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት እና ለኢትዮ ቴሌኮም ደብዳቤ መጻፉን መግለጹን አቶ ጥጋቡ አስታውሰዋል። 


የጋዜጠኛዋን “የሂሳብ እንቅስቃሴዎች ለማወቅ” ለ18 ባንኮች በተመሳሳይ ሁኔታ ደብዳቤ መላኩን የገለጸው ፖሊስ፤ ከተቋማቱ ምላሽ አስኪያገኝ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት መጠየቁንም አክለዋል።  


በችሎቱ ጋዜጠኛዋን ወክለው የተሟገቱት አቶ ጥጋቡ በበኩላቸው ፖሊስ “ሁሉን ነገር ጨርሷል። የብሔራዊ መረጃ ደህንነት አግልግሎት እና ኢትዮ ቴሌኮም እንዲሁም ባንኮቹ ግዙፍ የሆኑ ተቋማት ናቸው። በመረጃ አያያዝ እና ምስጢር ጠባቂነት መንግስት እና ህዝብ እምነት የሚጥልባቸው ናቸው። ደንበኛዬ [በተቋማቱ ላይ] ምንም አይነት ተጽዕኖ ልትፈጥር አትችልም” ሲሉ ደንበኛቸው በዋስትና እንድትወጣ መከራከሪያ ማቅረባቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። 


የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ፤ ጋዜጠኛ ሉዋም በአስር ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንድትፈታ በጥቅምት 26 ውሎው ወስኖ እንደነበር ጠበቃዋ አመልክተዋል።  የጋዜጠኛዋ ቤተሰቦች ከዕለቱ ችሎት መጠናቀቅ በኋላ የዋስትና ገንዘቡን ቢከፍሉም ጋዜጠኛዋ ሳትፈታ መቅረቷን አብራርተዋል። ቤተሰቦቿ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ይዘው በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ቢገኙም፤ ፖሊስ “ይግባኝ ስለጠየቅኩኝ [ትዕዛዙን] አልቀበልም” ብሎ ነበር ሲሉ ጠበቃዋ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ አስታውሰዋል።   


ከፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሶስት ቀናት በኋላ መርማሪ ፖሊስ “ስራዬን ስላልጨረስኩ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ይፈቀድልኝ” ሲል ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ይግባኝ ሰሚ ችሎት የይግባኝ አቤቱታ ማቅረቡን አቶ ጥጋቡ ገልጸዋል። በዕለቱ “በፍርድ ቤቱ ተመሳሳይ ክርክር አድርገን ነበር” የሚሉት የጋዜጠኛዋ ጠበቃ፤ ችሎቱ የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለቀጣዩ ቀን ቀጠሮ መስጠቱን ይጠቅሳሉ።   


በማግስቱ ማክሰኞ ጥቅምት 30፤ 2014 በዋለው ችሎት፤ የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ ማጽናቱን ተናግረዋል። ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ያስተላለፈው “መርማሪ ፖሊስ አሉኝ ያላቸውን ማስረጃዎች አሰባስቦ በማጠናቀቁ ተጨማሪ ጊዜ እንደማያስፈልገው” በመጥቀስ እንደሆነ ጠበቃዋ አስረድተዋል። 


ከፍርድ ቤቱ ውሳኔ በኋላ የሉዋም ቤተሰቦች እና ጠበቃዋ፤ ጋዜጠኛዋን ለማስፈታት ቢሞክሩም፤ ጥረታቸው ሳይሳካ ለሁለት ተጨማሪ ቀናት በእስር ቆይታለች።  


የአዲስ አበባ ፖሊስ ጋዜጠኛዋ ሐሙስ ዕለት መፈታቷን ለቤተሰቦቿ እና ለጠበቃዋ ቢገልጽም፤ ከእስር ሳትለቀቅ መቅረቷን ጠበቃዋ አቶ ጥጋቡ ተናግረዋል። 


ስለ ጉዳዩ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባላትን የጠየቁት ጠበቃዋ፤ “የፌደራል ፖሊስ ፈልጓት ሊሆን ስለሚችል የፌደራል ፖሊስን አናግሩ” የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው ይገልጻሉ።  


“የፌደራል ፖሊስን አናግር ባሉኝ መሰረት ሳናግር፤ ‘ሪፖርት ያደረገልን አካል የለም። የፍርድ ቤት ትዕዛዝም እኛ ጋር አልደረሰም’ አሉኝ” ሲሉ አቶ ጥጋቡ ሐሙስ ዕለት የገጠማቸውን አብራርተዋል። 


ጋዜጠኛዋ ላለፉት 21 ቀናት በእስር ወደ ቆየችበት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዓርብ ጠዋት የሄዱት ጠበቃዋ፤ “የፌደራል ፖሊስ በሌላ ጉዳይ ይፈልጋት እንደሆነ ማጣራት እንዲደረግ” በሚል ወደዚያው መላኳ እንደተነገራቸው ጠቅሰዋል። የፌደራል ፖሊስ ጋዜጠኛዋን በሌላ ጉዳይ እንደማይፈልጋት ካሳወቀ በኋላ፤ ሉዋም ትናንት ዓርብ ምሳ ሰዓት ገደማ ከእስር ተፈትታ ከቤተሰቦቿ ጋር መቀላቀሏን አቶ ጥጋቡ ተናግረዋል። 


ጋዜጠኛ ሉዋም ለእስር የተዳረገችው በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን የምትገኘው የሐይቅ ከተማ፤ በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር መዋሏን የሚገልጽ ዜና በመስራቷ ነበር። ጋዜጠኛዋ በቁጥጥር ስር የዋለችው ጥቅምት፤ 2014 ነበር። ከአራት ቀናት በኋላ ደግሞ ዜናው በተላለፈበት ዕለት ተረኛ አርታኢ፤ የነበረው ክብሮም ወርቁ በተመሳሳይ ሁኔታ በፖሊስ ተይዞ ወደ እስር ቤት ተወስዷል። 

አስተያየት ይለጥፉ

0 አስተያየቶች