የቀድሞው የፌስቡክ ሠራተኛ ፍራንሲስ ሐውገን፤ የፌስቡክን ሚስጥር አጋልጠዋል።
ፌስቡክ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎችም አገራት ሐሰተኛ መረጃ እና ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶችን እንዳላስቆመ በይፋ ተናግረዋል።
የአሜሪካ ኮንግረስ ፊት ቀርበው ቃላቸውን የሰጡት ፍራንሲስ ሐውገን፤ ፌስቡክ በኢትዮጵያ እና በምያንማር ግጭት ቀስቃሽ እና ሐሰተኛ መረጃዎችን ሳያስቆም ቀርቷል ብለዋል።
"እርምጃ የማይወሰድ ከሆነ አሁን ላይ የምናያቸው ጽንፈኛ ድርጊቶች እየተባባሱ ይሄዳሉ ብዬ እፈራለሁ። በኢትዮጵያ እና በምያንማር ያየናቸው ነገሮች ወደባሰ ደረጃ የሚደርሱ፣ የአስፈሪ ታሪክ የመጀመሪያ ምዕራፍ ናቸው" ብለዋል።
ፌስቡክ ሐሰተኛ መረጃዎችን፣ ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶችን እንዲሁም የጥላቻ ንግግሮችን ከመሰራጨት ማስቆም እንዳልቻለ ለኮሚቴው ተናግረዋል።
እአአ በ2018 ፌስቡክ በምያንማር ከተነሳው ነውጥ ጋር በተያያዘ የጥላቻ ንግግሮች እንዳይሰራጩ በማድረግ ረገድ ክፍተት መፍጠሩን አምኗል።
ከዚያ በኋላ በበቂ ሁኔታ የጥላቻ ንግግሮች እና ግጭት የሚቀሰቅሱ መልዕክቶችን ለመግታት ቃል ገብቶ ነበር።
የ37 ዓመቷ የቀድሞው የፌስቡክ ፕሮዳክት ማናጀር በአሜሪካ ምክር ቤት ተገኝተው ቃላቸውን ሲሰጡ ድርጅቱን በጽኑ ወቅሰዋል።
እንደ ፌስቡክ ያሉ ድርጅቶች፤ በገጻቸው ላይ በሦስተኛ ወገን ለሚለጠፉ መልዕክቶች ኃላፊነት እንዳይወስዱ የሚከላከላቸው የሕግ አንቀጽ 230 ላይ ለውጥ እንዲደረግም ፍራንሲስ ጠይቀዋል።
ፌስቡክ ለሚለጠፉት መልዕክቶች ኃላፊነት እንዲወስድ መደረግ እንዳለበት ለኮሚቴው ባደረጉት ንግግር ጠቁመዋል።
ፌስቡክን ተጠያቂ ማድረግ የሐሰተኛ መረጃ ስርጨትን እንደሚገታ አልፎም ግጭት እንዳይነሳ እንደሚከላከልም ተናግረዋል።
ፌስቡክ በአምባገነን እና የሽብር ድርጅት መሪዎች ጥቅም ላይ እየዋለ እንደሆነ በንግግራቸው አጋልጠዋል። እነዚህ አካሎች እየተጠቀሙበት እንደሆነ ፌስቡክ መረጃው እንዳለውም አክለዋል።
የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ላይክ እና ሼር እንዲያደርጉ እንዲሁም አስተያየት እንዲሰጡ የሚያነሳሱ ጽሑፎች በገጹ ወደላይ እንደሚገፉ ተናግረዋል።
"እነዚህ መልዕክቶች እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በብሔር ክፍፍል የሚናጡ አገሮች ውስጥ ግጭት እያስነሱ ነው" ሰሉም አብራርተዋል።
ፌስቡክ ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶችን ለማቀብ የተለያዩ አሠራሮች ቢዘረጋም ካለው ችግር አንጻር እርምጃው በቂ እንዳልሆነ እና ከእንግሊዘኛ ውጪ ባሉ ቋንቋዎች የሚጻፉ መልዕክቶችን በማጥራት ረገድ ሰፊ ክፍተት እንዳለበት ተናግረዋል።
"ፌስቡክ ተጠቃሚዎቹን በገጹ ላይ የሚያቆይ መልዕክትን በአጠቃላይ ወደ ገጹ ፊት ማምጣት ተገቢ እንዳልሆነ ተናግሯል። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ግጭት የሚነሳው በእነዚህ ጽሑፎች ሳቢያ ነው። መልዕክቶች መመዘን ያለባቸው በይዘታቸው ነው" ሲሉ አብራርተዋል።
የቀድሞዋ የፌስቡክ ሠራተኛ ፍራንሲስ ሐውገን ያደረጉትን ንግግር ተከትሎ ድርጅቱ፤ ንግግሩን ውድቅ የሚያደርግ ምላሽ ሰጥቷል።
የፌስቡክ ቃል አቀባይ አንዲ ስቶን በትዊተር ገጻቸው እንዳሉት፤ ፍራንሲስ በድርጅቱ ውስጥ የሠሩት ለሁለት ዓመታት ብቻ ከመሆኑ ባሻገር ሪፖርቶችን በቀጥታ የሚያገኙበት መንገድ አልነበራቸውም ብለዋል።
"ውሳኔ የሚተላለፍባቸው ስብሰባዎች ላይ ተሳትፈው አያውቁም። በሕግ አውጭ ኮሚቴ ጥያቄ በቀረበባቸው ጉዳዮች ላይ በቅርብ እንዳልሠሩም ተናግረዋል" ብለዋል ቃል አቀባዩ።
'ፌስቡክ' በበኩሉ የቀድሞ ሠራተኛው ስለ ድርጅቱ በተናገሩት ነገር እንደማይስማማም ቃል አቀባዩ አክለዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
0 አስተያየቶች