Ticker

6/recent/ticker-posts

በሁሉም የአማራ ክልል ከተሞች የእንቅስቃሴ ገደብ ተጣለ

የእንቅስቃሴ ገደቡ የተጣለው ዛሬ እሁድ ጥቅምት 21 ቀን 2014 ዓ.ም አስቸኳይ ስብሰባውን ባደረገው የክልሉ ምክር ቤት ነው።

"ወራሪው" የህወሓት ኃይል በአማራ ክልል ሕዝቦች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት እየፈፀመ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የመጨረሻ የሞት ሽረት ትግል እያደረገ ነው ያለው ምክር ቤቱ የተደቀነውን የህልውና አደጋ በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ብቻ መቀልበስና ማሸነፍ የማይቻል ሆኖ መገኘቱን በማስታወቅ የተለያዩ የአስቸካይ ጥሪ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

በውሳኔው መሠረትም ምክር ቤቱ መደበኛው የመንግስት ተቋማት አገልግሎት ተቋርጦ የገጠሙ የህልውና ችግሮችን ለመቀልበስ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ርብርብ እንዲደረግ እና በጀት ጭምር ለዚሁ ዓላማ እንዲውል፣

ሁሉም የመንግስት ተሽከርካሪዎች ወደ አንድ ማዕከል ተሰባስበው ለሕልውናው ዘመቻው አገልግሎት እንዲውሉና የግል ተሸከርካሪ ባለቤቶች በተፈለጉ ጊዜ ሁሉ ተሽከርካሪዎቻቸውን በመስጠት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ፣

የየደረጃው አመራር የሕልውና ዘመቻውን ተቀብሎ የሚሰለፈውን ሕዝብ አደራጅቶ ከፊት ሆኖ እየመራ ወደ ግንባር እንዲዘምት፤ ይህን በማያደርጉ አመራሮች ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ወስኗል።

ሁሉም የመንግስትና የግል የጦር መሳሪያ የታጠቀ በሙሉ ለሕልውና ዘመቻው አገልግሎት እንዲውል ያለም ሲሆን ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ማንኛውም የግል መሳሪያ ታጥቆ በማንኛውም ምክንያት በሕልውና ዘመቻው ላይ የማይሳተፍ የክልሉ ነዋሪ

የታጠቀውን የግል መሳሪያ በአደራ ለመንግስት እንዲያስረክብ ወይም እድሜው ለትግል ለደረሰ እና አካላዊ ጤንነት ላለው ለቤተሰብ አባሉ ወይም ለሌላ ሰው በማስተላለፍ ለህልውና ዘመቻው አገልግሎት እንዲውል እንዲያደርግ አዟል።

ሕዝቡ የሚያስፈልገውን የሎጂስቲክስ አገልግሎት በማቅረብ የሕልውና ዘመቻውን ውጤታማ እንዲያደርግ፣ በየደረጃው የሚገኘው አመራርም አቅርቦቱ የተሳለጠ እንዲሆን አስፈላጊውን እንዲፈጽም እንዲሁም የሕልውና ዘመቻውን ተቀብሎ በግንባር ለመፋለም ከሚሰማሩት ውጭ ያለው ማንኛውም የክልሉ ነዋሪ በየአካባቢው ተደራጅቶ የአካባቢውን ጸጥታ እንዲጠብቅ፣ ጸጉረ ለውጦችንና ሰርጎ ገቦችን እንዲከታል እና ለሕግ አስከባሪ አካላት አሳልፎ በመስጠት የበኩሉን ኃላፊነት ሁሉ እንዲወጣም ወስኗል።

የህልውና ዘመቻውን ውጤታማ ለማድረግ በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ለትግሉ በተለያየ መንገድ እንቅፋት በሚሆን ማንኛውም ሰው ወይም ቡድን ላይ በየደረጃው እየተወሰነ የጸጥታ አካሉ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ የወሰነው ምክር ቤቱ የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዲሰጡ ከተፈቀደላቸው ተቋማት ውጭ በሁሉም ከተሞች ከምሽቱ 2፡00 በኋላ እንቅስቃሴ ማድረግ አይቻልም ብሏል።

እነዚህን ዘጠኝ አስገዳጅ ውሳኔዎች ዝርዝር አፈጻጸም በተመለከተ በክልል ደረጃ በተቋቋመው የዘመቻ መምሪያ በሚቀመጥ አሰራር የሚወሰን እንደሚሆንም ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡


አል ዐይን ኒውስ

አስተያየት ይለጥፉ

0 አስተያየቶች