በአማራ ክልል የደቡብ ወሎ ዞን ዋና ከተማ ከሆነችው የደሴ ከተማ የፌደራሉ ሠራዊት ማፈግፈጉንና በህወሓት የሚመሩት የትግራይ ኃይሎች መግባታቸው መዘገቡን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ከተማዋ አሁንም በቁጥጥሬ ስር ናት ይላል።
በሌላ መልኩ የትግራይ ኃይሎችን የሚመራው ሕወሓት ደሴን ተቆጣጥሬአለሁ ሲል ይገልፃል።
ቢቢሲ አማርኛ ቅዳሜ ረፋድ ላይ አነጋግሬያቸዋለሁ ያላቸው የደሴ ከተማ ነዋሪዎች የትግራይ ኃይሎች ወደ ከተማዋ ሲገቡ መመልከታቸውንና የመንግሥት ኃይሎች ማፈግፈጋቸውን ገልፀዋል።
በተጨማሪም "የትግራይ መከላከያ ኃይል" በመባል የሚጠሩትና የፌደራሉ መንግስት "አሸባሪ" ሲል የሚጠራቸው የትግራይ ኃይሎች ወደ ሰኞ ገበያ፣ ተቋም እና ሳላይሽ አካባቢዎች ሲያመሩ እንደታዩና በከተማዋ ዳርቻ አካባቢ ተኩስ እንደሚሰማ ነዋሪዎቹ ገልፀዋል።
በከተማዋ አንዳንድ ቦታዎች ከአርብ ጀምሮ የኤሌትሪክ አገልግሎት መቋረጥ የገጠመ ሲሆን ዛሬ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ጀምሮ ደግሞ የስልክ አገልግሎት ተቋርጧል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሶ "አሁንም ደሴና አካባቢዋ በመንግሥት የፀጥታ ኃይል ስር ናቸው" ብሏል።
ሮይተርስ የሕወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳን ጠቅሶ የትግራይ ኃይሎች የመንግሥት ሠራዊትን ከደሴ ከተማ ገፍቶ በማስወጣት ከተማዋን መቆጣጠራቸው ካልተጠቀሰ ቦታ በሳተላይት ስልክ እንደነገሩት ዘግቧል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የህወሓት ኃይሎች ሌሊቱን ሙሉ ደሴን ለመያዝ በተለያዩ መስመሮች ጥቃት ማካሄዳቸውን በመግለፅ በአካባቢው ያለው የመንግሥት የፀጥታ ሃይል ጥቃቱን መመከቱን እና የፀረ ማጥቃት እርምጃ መቀጠሉን በመግለጫው አመልክቷል።
ኤኤፍፒ በበኩሉ ነዋሪዎችን ጠቅሶ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ እንደዘገበው የኢትዮጵያ መንግሥት ኃይሎች ከደሴ ከተማ ማፈግፈጋቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች እንደነገሩት ዘግቧል።
ጨምሮም ከባድ ውጊያ ከተካሄደ በኋላ በከተማዋ አንዳንድ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጡን ዜና ወኪሉ አመልክቷል።
የትግራይ ኃይሎች በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ በጦርነት የተፈናቀሉ ሰዎች የሚገኙባትን ቁልፍ ከተማ ደሴን መቆጣጠራቸውን ለሮይተርስ የነገሩት አቶ ጌታቸው ረዳ ተዋጊዎቻቸው ወደ ኮምቦልቻ እያመሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ግን የህወሓት ኃይሎች ደሴን እንዳልያዙ በመጥቀስ "ያለውን ኃይል ሁሉ አሰባስቦ በጦር ግንባር ያቃተውን በወሬ ለማግኘት አሁንም መፍጨርጨሩን ቀጥሏል" ሲል ዜናውን አጣጥሎታል።
ሮይተርስ እና ኤኤፍፒ አናገርናቸው ያሏቸው የደሴ ከተማ ነዋሪዎች የመከላከያ ሠራዊቱ ቅዳሜ ጠዋት ከከተማዋ በመውጣት ወደ ኮምቦልቻ ሲያመሩ መመልከታቸውን ተናግረዋል።
አንድ የትምህርት ቤት ዳይሬክተር እና አንድ ነዋሪ የፌደራሉ ሠራዊት አባላት ሲወጡ እንዳዩና በከተማዋ የኤሌክሪክ ኃይል ከአርብ ጀምሮ መቋረጡን እንዲሁም የህወሓት ኃይሎች መግባታቸው ሲነገር ቢሰሙም እንዳላዩ ለሮይተርስ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በደሴ ከተማና በአካባቢዋ ስላላው ሁኔታ ባወጣው መግለጫ በአገሪቱ ሠራዊት የሚመራው ኃይል የትግራይ ኃይል ጥቃትን እየመከተ የፀረ ማጥቃት ዘመቻ እያካሄደ ነው ብሏል።
ከአዲስ አበባ 385 ኪሎ ሜትር የምትርቀው የደሴ ከተማ በአማራ ክልል ውስጥ ካሉ ትልልቅ ከተሞች መካከል አንዷ ስትሆን የደቡብ ወሎ ዞን ዋና ከተማ ናት።
በትግራይ ውስጥ የተቀሰቀሰው ጦርነት ወደ አማራ እና አፋር ክሎች ከተስፋፋ በኋላ ከሰሜን ወሎ በጦርነቱ የተፈናቀሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በከተማዋ ተጠልለው ይገኛሉ።
ከቀናት በፊት መንግሥት ሽብርተኛ የሚለው የህወሓት ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ደሴ እና ኮምቦልቻን ለመቆጣጠር ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን በመጥቀስ የከተማዎቹ ነዋሪዎች ከቤት እንዳይወጡ ተዋጊዎችም እጃቸውን እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበው ነበር።
ከሁለት ሳምንት በፊት መልሶ ያገረሸው ውጊያ በአማራና በአፋር ክልሎች እየተካሄደ ሲሆን በተለይ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ውስጥ ከባድ ውጊያ እየተካሄደ ቀናት ተቆጥረዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይልም በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች የህወሓት ኃይሎች ይጠቀሙባቸዋል ያላቸው ስፍራዎች ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሙ በተከታታይ ተዘግቧል።
በዚህም ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸውን የሆስፒታል ምንጮች እና የህወሓት ኃይሎች ቢገልጹም መንግሥት ግን ዒላማዎቹ የተመረጡና ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በጥንቃቄ የተካሄዱ የአየር ጥቃቶች መሆኑን በመግለጽ አስተባብሏል።
በመቐለ ከተማ በተደረገ ተደጋጋሚ የአየር ጥቃት ከ10 በላይ ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸው የተንቀሳቃሽ ምስሎችን በማስረጃነት በማቅረብ ትግራይ ቴሌቪዥን መዘገቡ ይታወሳል።
0 አስተያየቶች