Ticker

6/recent/ticker-posts

የተመድ እና የኢሰመኮ የጦርነት ምርመራ ሪፖርት ጥቅምት 24 ይፋ ይሆናል

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በጋራ በትግራይ ክልል በተካሄደው ጦርነት የደረሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ላይ ሲያደርገው የነበረው ምርመራ ረቡዕ ጥቅምት 24 ቀን 2014 ዓ/ም ይፋ እንደሚሆን አስታወቀ፡፡ 
ሰኞ ጥቅምት 22 ቀን 2014 ዓ/ም ይፋ ይደረጋል ተብሎ የነበረው የጋራ ጥናቱ በትግራይ ክልል በኩል "ኢሰመኮ ለመንግሥት ይወግናል" የሚል ተቃውሞ ተነስቶበት እንደነበር አይዘነጋም።

አንድ አመቱን ሊደፍን የቀናት ዕድሜ በቀረው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ለመፈናቀልና ረሀብ ሲዳርግ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎችም ተገድለዋል። 
በትግራይ ክልልና በፌደራል መንግሥት መካከል የተነሳው ጦርነቱ ሃገራት በቀጥታም በተዘዋዋሪም ተሳታፊ መሆናቸው ተረጋግጧል። 
በመሆኑም ተቋማቱ በጦርነቱ ወቅት ተፈፅመዋል የተባሉ የግድያ፣ የአስገድዶ መድፈርን እና ሌሎችንም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በጋራ መርምረዋል፡፡ 
ከፈረንጆቹ ግንቦት 16 እስከ ነሀሴ 20 ቀን 2021 ድረስም ከ200 በላይ ሰዎችን ቃለመጠይቅ ማድረጋቸውን ገልፀውም ነበር፡፡ 
የምርመራው የመስክ ስራ በመቐለ፣ ውቅሮ፣ ሳምረ፣ አላማጣ፣ ቦራ፣ ማይጨው፣ ዳንሻ፣ ማይካድራ፣ ሑመራ፣ ጎንደር፣ ባህርዳር እና አዲስ አበባ ከተሞች እንደሆነ ኢሰመኮ ገለጿል፡፡

በምርመራው በግጭቱ የተጎዱ ሰዎች፣ የአይን ምሰክሮች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት እንዲሁም የክልል እና የፌደራል ተቋማት ሰራተኞች፤ አመራሮች፣ የህክምና ባለሙያዎች፣ የፍትህ አካላት እና ሌሎች ስለ ጉዳዩ ያውቃሉ የተባሉ አካላት ተጠይቀዋል፡፡ 
የምስል እና የሰነድ ማስረጃዎች፣ ቪዲዮዎችን እና ሌሎች ለምርመራ ይጠቅማሉ የተባሉ መረጃዎችን ሁሉ ተሰባስበዋል ተብሏል።


አስተያየት ይለጥፉ

0 አስተያየቶች